ፓርቲው የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብለው እንደሚያምኑ የጋምቤላ ወጣቶች ገለጹ

92

ኢዜአ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የብልጽግና ፓርቲ የወጣቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት በተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ገለጹ። በፓርቲው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ላይ ውይይት ያደረጉ ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት ፓርቲው ወጣቶችን ይበልጥ አሳታፊ በማድረግ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታውን ያሳድጋል የሚል እምነት እንዳለቸው ተናግረዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት መንግስቱ ላላጎ በሰጠው አስተያየት በውይይቱ የፓርቲው ፕሮግራም ለወጣቱ ተጠቀሚነትና ተሳታፎ ተገቢ ትኩረት ስለመስጠቱ ግንዛቤ መያዛቸውን ተናግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው ለአገር ልማት፣ እድገትና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ለወጣቱ በሚፈለገው መንገድ ትኩረት ይሰጥ እንዳልነበር አስታውሷል።

"የፓርቲው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ሁሉንም ክልሎች ያለ ልዩነት በአንድነት ያቀፉ በመሆኑ ተስፋ የሚሰጥ ነው" ያለው ደግሞ ሌላው ተሳተፊ ወጣት ኡማን ኦኬሎ ነው ።

ቀደም ሲል በነበረው የኢህአዴግ አሰራር በትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አጋር ድርጅቶች እኩል ተሳትፎና የመወሰን መብት እንዳይኖራቸው አባልና አጋር ድርጅቶች በሚል ልዩነት እንደነበር አስታውሰዋል።

"አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ ለወጣቱ ፍላጎትና ተጠቃሚነት ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን በፓርቲው ፕሮግራም ላይ ባካሄድነው ውይይት መረዳት ችያለሁ" ያለው ደግሞ ሌላው ወጣት ኬት ዴር ነው።

ከዚህ በፊቱ ለወጣቱ ተገቢ ትኩርት ባለመሰጠቱ ወጣቶች ብዙም ተጠቃሚ እንዳልሆኑና ዛሬም ችግሮቻቸው አለመፈታታቸውን ተናግሯል ።

የብልግጽና ፓርቲ ለወጣቱ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ለውጥ በትኩረት እንደሚሰራ ከፓርቲው ፕሮግራም መገንዘብ እንደቻለ የገለጸው ደግሞ መምሰል ቲሞቲዎስ የተባለ የከተማዋ ወጣት ነው።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ፓርቲው በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ውጤታማነት ከፓርቲው ጎን በመሰለፍ የበኩላቸው አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

የጋምቤላ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ላይ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም