የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ነገ ይጀመራል

80

ታህሳስ  3/2012 የሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል የ2012 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም ይጀመራል። ፕሪሚየር ሊጉ ህዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲጀመር ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም በ14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዝግጅት ምክንያት ለአንድ ሳምንት እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት የፕሪሚየር ሊጉ መክፈቻ አዲስ አበባ ፖሊስ ከመከላከያ ከጠዋቱ ሦሰት ሰዓት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል።

ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም ከጠዋቱ 2፡30 ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር ይጫወታሉ።

በክልል ከተሞች ሶዶ ላይ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ከአዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሶዶ ላይ የሚያካሂድ ሲሆን ሙገር ሲሚንቶ ከጣና ባህርዳር በተመሳሳይ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ሙገር ላይ ይጫወታሉ።

የአምና የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ የነበረው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ቢፈርስም ዘንድሮ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በሁለቱም ጾታዎች ቡድን በማቋቋሙ በፕሪሚየር ሊጉ ይወዳደራል።

የ2012 ዓ.ም የሀበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ እንዲካሄድ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብሩህ ተክለማርያም በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከጌታ ዘሩ ስፖርት ክለብ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ፕሪሚየር ሊጉን በተያዘው ወር ለመጀመር ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

የዘንድሮው ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛው የውድድር ዓመት ነው።

ወላይታ ድቻ አራት፣ ሙገር ሲሚንቶ ሦስት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱም ጾታዎች እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም