በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተስተጓጉሎ የነበረው የመማር ማስተማር ሥራ ተጀመረ

93
ጋምቤላ ግንቦት 1/2010 በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል ተከስቶ የነበረው አለመግባባት እልባት በማግኘቱ ለቀናት ተስተጓጉሎ የነበረው የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ። ተማሪዎች በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ትምህርታቸውን መከታተል እንደጀመሩ ገለጸዋል። የዩኒቨርሲቲው የሕዝብና የውጪ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ቶማስ ቱት ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በተቋሙ ሚያዝያ 24 ቀን 2010 በተማሪዎች መከካል በተፈጠረው አለመግባባት ለቀናት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሥራ ትናንት ተጀምሯል። የዩኒቨርሲተው አመራሮችና ተማሪዎች ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት በጋራ ተወያይተው ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ የመማር ማስተማሩ ሥራ ወደ ቀድሞው ሂደት መመለሱን ነው የተናገሩት። ከተማሪዎች መካከል ተማሪ ይታይህ አዝመራው በሰጠው አስተያይት በተማሪዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ቅራኔ በትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች፣ በዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጥረት ተወግዶ ትምህርታቸውን መከታተል እንደጀመሩ ተናግሯል። በዩኒቨርሲቲው ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ተማሪ ፒተር ሬስ ነው። ተማሪ ነገሰ ፍቅሩ በበኩሉ ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው ግጭትና በዩኒቨርሲው በካፍቴሪያ፣ በጥበቃ አካላት፣ በመማር ማስተማርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በተስተዋሉ የመልካም አስተዳድር ችግሮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸጿል ። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ያሉበትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሆነ በተማሪዎች መካከል ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ ሥራዎችን መስራት እንዳለበት ተናገሯል። የዩኒቨርሲቲው የሕዝብና የውጪ ግንኙነት ዳሬክተሩ አቶ ቶማስ ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በተማሪዎች የተነሱት ጥያቄዎች አግባብነት ያለቸው መሆኑን አምነው በአጭር ጊዜና በሂደት የሚፈቱ ችግሮች ተለይተው ለመፍትሄው ወደሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
Published in ማህበራዊ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም