በጋምቤላ ክልል ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል አመራሩ ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ተመለከተ

57
ታህሳስ 3/2012 በጋምቤላ ክልል የሙስናና ብልሹ አሰራር ን ለመከላከል በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ ''መልካም ስነ ምግባር በመገንባትና ሙስናን በመታገል ዘላቂ ሰላምና ልማት እናረጋግጥ'' በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም የጸረ ሙስና ቀን በጋምቤላ ከተማ  በፓናል ውይይት ተከብሯል። የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት እየተስፋፋ የመጣው የሙስናና የብልሹ አሰራርን ለማስወገድ  በተለይም በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ግንባር ቀደም ኃላፊነት አለባቸው። ከተሳታፊዎች መካከል መምህር አበራ ደመና በሰጡት አስያየት ''ሙስናና ብልሹ አሰራሮች እየተፈጸሙ ያሉት በከፍተኛ በአመራሮች ፣ በባለሃብቶችና ተምረናል በሚሉ አካላት ነው'' ሲሉ ገልጸዋል። ችግሩ በሀገሪቱ ልማት ላይ እያደረሰ ካለው ተጽዕኖ ባሻገር እየታየ ላለው የሰላም እጦት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል። ይህንን ችግር ለማስወገድ በተለይም አመራሩ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ሊወጣ እንደሚገባ አመልከተዋል። የሙስናና የብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል ጥረት ቢደረግም እስካሁን በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ሊመጣ እንዳልቻሉ የገለጹት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ አንድሮው ቱት ናቸው። እያንዳንዱ አመራር ከሚመራው ተቋም ጀምሮ ሙስናን ለማጽዳት አረአያ በመሆን ሊሰራ ይገባል "ብልዋል። ሌላው ተሳታፊ አቶ ጥበቡ በቀለ በበኩላቸው  በክልሉ ስልጣን መከታ በማድረግ  ብልሹ አሰራሮች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይም በክልሉ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች እንደሚቸበሰቡ ጠቁመው የክልሉ መንግስትም ሆነ ፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ችግር ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም መሆኑን ገልጸዋል። ችግሮች ለማስቀረት በተለይም አመራሩና ፀረ- ሙስና ኮሚሽኑ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የክልሉ ስነ- ምግባርና ፀረ- መስና ኮሚሽነን ኮሚሽነር አቶ ሳይመን ቱሪያል ሙስናና የብልሹ አሰራር በአመራሩ ብቻ ሊስተካከል እንደማይችል ተናግረዋል። ለፀረ- ሙስና ትግሉ ውጤታማነት የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ እንደሚያሰፈልግ አመልክተዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳዳር ተወካይ ዶክተር ሎው ኡቡፕ "ሙስና ያልተመጠነ የሀብት ክፍፍል የሚታይባት አጋጣሚ ስለሆን ለአንድ ሀገር ግጭት መንስኤ ነው" ብለዋል። ችግሩን ለመከለከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንዳሚገባ አሳሰበዋል። የክልሉ ስነ- ምግባርና ፀረ- ሙስና ከሚሽን ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የፓናል ውይይት  ከ300 በላይ የአመራር አካላት፣ ተማሪዎችና የሲቪክ ማህበራት ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም