የተቋማት አለመናበብ የመንገድ ግንባታዎችን እያጓተተ መሆኑ ተነገረ

63
ኢዜአ  ታህሳስ 3 /2012 -- የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት አለመናበብና በቅንጅት አለመስራታቸው በመንገድ ግንባታዎች ላይ መጓተት እያስከተለ መሆኑን የፌደራል የተቀናጀ መሰረተ ልማቶች አስተባባሪ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ችግሩን ለመፍታት  ያዘጋጀው የሁለት ቀን የውይይት መድረክ ከትላንት ጀምሮ በመቀሌ እየተካሄደ ነው ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማው መንግስቴ እንደገለጹት የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሀ ጨምሮ ሰባት ተቋማት ተናበውና ተቀናጅተው ባለመስራታቸው የመንገድ ግንባታዎች  እስከ አምስት አመት የሚጓተቱበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። የግንባታ ስራቸው እሰከ መቆም የሚደርሱ መንገዶችም መኖራቸውን ተናግረዋል ። በተቋማቱ አለመናበብ እንደ ሀገር የ82 መንገዶች ግንባታ መጓተቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ። በመንገድ ግንባታዎች መጓተትም ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑን ጠቅሰዋል ። ተቋማቱ በመናበብና በመቀናጀት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እዲጠናቀቁ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል ። "በኤሌክትርክ፣ ውሃ፣ መንገድና ቴሌኮም ያለው የአሰራር ችግር ካልተፈታ ፈጣን የመንገድ ልማት ለማምጣት  አይቻልም" ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል ኮንስትራክሽን፣ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ገብረፃዲቅ ናቸው። ተቋማቱ የፌደራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማቶች አስተባባሪ ኤጀንሲ  ያወጣውን አሰራርና ደንብ ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል። በውይይት መድረኩ ከኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከውሀ፣ መንገድ ትራንስፖትና ሌሎች ተቋማት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም