ገንዘብና የሰው ጉልበት የፈሰሰባቸው የምርምር ውጤቶች አብዛኛዎቹን ፖሊሲ አውጭዎች አይጠቀሙባቸውም

72
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች አገራዊ ችግሮችን ይፈታሉ በሚል ገንዘብና ጉልበት ፈሶባቸው የሚካሄዱ ምርምሮች ፖሊሲ አውጪዎች እንደማይጠቀሙባቸው ተገለጠ። በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ስራ ላይ እንዲውሉ ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የግልና የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ምሁራን የሚሳተፉበት 17ኛው "ሁሉን አቀፍ የጥናትና ምርምር ዓመታዊ ኮንፈረንስ" በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ዛሬና ነገ በሚከናወነው ኮንፈረንስ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በቢዝነስና መሰል አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ከ20 በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች ይቀርባሉ ተብሏል። የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀኑ ሲሳይ እንዳሉት፤ ችግር ፈቺ ተብለው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና የሰው ጉልበት የፈሰሰባቸው የምርምር ውጤቶች አብዛኞቹ ፖሊሲ አውጭዎች ሳይጠቀሙባቸው መደርደሪያ ሲያሞቁ ይስተዋላል። የግል ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋቋሙበት ዓላማ አንዱ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናዎን ለፖሊሲ አውጪዎች ማቅረብ በመሆኑ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ እየሰራበት እንደሆነ ጠቁመዋል። እስካሁን በዩኒቨርሲቲው የህትመት ዘርፍ በማቋቋም የጥናትና ምርምር ውጤቶች ታትመው ለፖሊሲ አውጪዎች እንዲደርሱ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። በግል ዩኒቨርሲቲዎች መምህርና አማካሪ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ ደመረ በኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጭዎች ዘንድ የጥናትና ምርምር ውጤቶች የመጠቀም ልምዳቸው አናሳ መሆኑን ተናግረዋል። “በጥናትና ምርምር ውጤቶች ያልተደገፈ ፖሊሲና ስትራቴጂ አጥጋቢ ውጤት ስለማያስገኝ መንግስት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል'' ብለዋል። ባለፉት 17 ዓመታት በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ስራዎች በብዛት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንዳልሆነ አስረድተዋል። “የምርምር ውጤቶቹ በፖሊሲ አውጪዎቹ አማካኝነት ስራ ላይ እንዲውሉ አለመደረጋቸው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ይጎዳል፤ ኅብረተሰቡ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ያሳጣል፤ የሰው ጉልበት ያለ አግባብ እንዲባክን ያደርጋል ነው'' ያሉት። በመሆኑም የአገሪቱ ፖሊሲ አውጪዎች ከምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለአገሪቱ ቀጣይነት ያለው እድገት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም