ሆስፒታሉ በተሰጠው ነጻ የዓይን ህክምና አገልግሎት 1 ሺህ 300 ሰዎች ተጠቃሚ ሆኑ

60

ኢዜአ ታህሳስ 3/2012 የኩኃ የዓይን ህክምና ሆስፒታል ለአንድ ሳምንት ባካሄደው ነጻ የዓይን ህክምና አገልግሎት በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ አንድ ሺህ 300 ህሙማን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ።

ሆስፒታሉ ነጻ የህክምና አገልግሎቱን የሰጠው አሜሪካ ከሚገኘው እና  ‘’ሂማሊያ ካታራክት’’ ተብሎ ከሚታወቀው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባባር ነው።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚኪኤለ ሐጎስ ለኢዜአ እንዳሉት ከህዳር 24ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምን በተካሄደው ነጻ የህክምና አገልግሎት ለህሙማኑ የዓይን ሞራና የዓይን ጸጉር ቀዶ ህክምና ተደርጎላቿዋል።

እንዲሁም በትራኮማ በሽታ የተጠቁ ህሙማንም ተገቢውን ምርመራና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልጸዋል።

 ሆስፒታሉ ከግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጋር በመተባበር በየዓመቱ በትግራይ ክልል 60 በመቶ በዓይን በሽታ ይጠቃሉ ተብሎው በተለዩ ወረዳዎች በመዘዋወር ነጻ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከህክምና አገልግሎቱ ጎን ለጎን ለዓይን በሽታ መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችና ችግሮችን በመለየት ህብረተሰቡ ራሱን አስቀድሞ እንዲከላከል የግንዛቤ ማሳደግያ ትምህርት እንደሚሰጡም አስታውቀዋል፡፡።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተካሄደ ነጻ የህክምና አገልግሎት  በትግራይ ክልል 50 ሺህ ያህል ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በማድረግ ከዓይን ስውርነት አደጋ አስቀድመው መከላከል እንዲችሉ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

የዓይን ስውርነት በሽታ በአብዛኛው የሚከሰተው በዓይን ፀጉር መታጠፍ፤ ሞራና ትራኮማ በሽታዎች ምክንያት መሆኑን ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

ሰሞኑን በተካሄደው ነጻ የዓይን ህክምና ዘመቻ ተጠቃሚ ከሆኑ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች መካከል የ75 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ እና የሰሓርቲ ሳምረ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ፍቓዱ ሃይሉ አንዱ ናቸው።

በድንገት የዓይን ሞራ ጋርዶሽ ለሁለት ዓመታት ያህል ብርሃኔን አጥቼ በሰው እየተመራሁ እንቀሳቀስ ነበር ያሉት አርሶ አደር ፍቃዱ፣ ወደ ኩሓ የዓይን ሆስፒታል ሄደው በመታከማቸው የዓይን ብርሃናቸውን እንደተገለጠላቸው ተናግረዋል።

በፀጉር መታጠፍ ምክንያት ተሸፍኖ የነበረውን ዓይኔ በህክምና ድጋፍ እንዲገለጥልኝ በመደረጉ ለማየት በቅቻለሁ ያለው ደግሞ በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን የእደርታ ወረዳ ነዋሪ ወጣት መሐሪ ሙሉ ነው።

ከዓፋር ክልል አብዓላ ወረዳ መጥተው የዓይን ሞራ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው የ60 ዓመቱ ሓጂመሓመድ  ዓብደላ በበኩላቸው፣ በተደረገላቸው የህክምና ድጋፍ ለማየት መብቃታቸውን ከልብ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም