የሰበታ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከሜታ ቢራ ፋብሪካ ጋር የ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረመ

75
ኢዜአ ታህሳስ 3/2012 የሰበታ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከሜታ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለአራት ዓመታት የሚቆይ የ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረመ። በክለቡና በፋብሪካው መካከል የተደረገው ስምምነት 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እና 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የስፖርት ቁሳቁስን ያካተተ ነው። የሰበታ እግር ኳስ ክለብ በማሊያው ላይ የሜታ ቢራ ፋብሪካን ስም በማሳተም የሚያስተዋውቅ መሆኑንም በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል። እንዲሁም የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ወደፊት ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም የፋብሪካውን ምርቶች  በክለቡ በኩል ለማስተዋወቅ ዕቅድ እንዳለም ተገልጿል። የሜታ ቢራ ፋብሪካ ለስፖንሰርሺፕነት ያበረከተውን ገንዘብ በየዓመቱ ለክለቡ የሚያበረክት ይሆናል። በተያዘው በጀት ዓመት የሰበታ ከተማ እግር ኳስ ክለብ እያስገነባ ላለው ስታዲየም ግንባታ የሚውል 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ፋብሪካው ለክለቡ ያበረክታል። በ2013 ዓ.ም ሦስት ሚሊዮን ብር ለክለቡ ክፍያ የሚፈጸም ሲሆን በ2014 እና በ2015 ዓ.ም ቀሪ ስምንት ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደሚፈጸም በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም