የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ለተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ተባለ

128
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ለተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ተባለ። የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች ነገ በአገርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተከብሮ የሚውለውን የሲቪል ሰርቪስ ቀን በሚመለከት ባደረጉት ውይይት ቢሮው የደንበኞቹን ፍላጎት ማሟላት እንዳልቻለ ተገልጿል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳምጠው አበበ ለውይይቱ መነሻነት ባቀረቡት ጹሁፍ እንዳመለከቱት፤ ቀልጣፋ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት ተገልጋዮች በወቅቱ ጉዳያቸው እየተፈጸመላቸው አይደለም። በተቋሙ የሙስና ችግርና የሀብት ብክነት እንደሚስተዋል እንዲሁም ሰራተኞች ስራቸውን በባለቤትነት ስሜት እየሰሩ አለመሆኑ ተነግሯል። የሰራተኛውን ጥቅም የሚያስጠብቅ ፍትሀዊና ግልጽ አሰራር ባለመኖሩ ሰራተኞች ስራቸውን በባለቤትነት ስሜት እንዳይሰሩ ምክንያት እንደሆነ የቢሮው ሰራተኞች ተናግረዋል። ለተመሳሳይ ስራ የተለያየ ክፍያ መኖር የሰራተኞች የእድገትና የቅጥር ሁኔታ ያለ ውድድር ግልጽ ባልሆነ መንገድ መፈፀሙ የሰራተኛውን የስራ ተነሳሽነት እንደጎዳው ሰራተኞቹ ተናግረዋል። በከተማዋ ለሚገኙ ከ300ሺህ በላይ ነጋዴዎች አሁን ያለው የንግድ ቢሮ ሰራተኞች ቁጥር ከዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ብዙም ልዩነት የሌለው በመሆኑ ደንበኞች ለእንግልት የተዳረጉበት ሌላ ምክንያት መሆኑንም ሰራተኞቹ  ገልጸዋል። የቢሮው ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ለተመሳሳይ ስራ የተለያየ ክፍያ መኖሩ የሰራተኞችን የስራ ተነሳሽነት እየጎዳ እንደሆነ ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ቀርቦ መፍትሄ ለማግኘት እየተሞከረ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በመዲናዋ የነጋዴዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመሆኑ አሁን ያለው የሰራተኞች ቁጥር በቂ ባለመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ጥናት መደረጉን አስታውቀዋል። በ2003 ዓ ም 84 ሺህ ብቻ  የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ የነጋዴዎች ቁጥር አሁን ከ300 ሺህ በላይ በመድረሱ ከሰባት ዓመታት በፊት የነበረው ጥናት እንደገና ተጠንቶ የሰራተኞችን ቁጥር ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል። ''ህዝብን በቀናነት ማገልገል ድርብ ክብር ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ የፐብሊክ ሰራተኞች ቀን ነገ ይከበራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም