ለአገሪቷ የንግድ መስፋፋትና የኢንዱስትሪ ልማት እድገት የሴቶች ተሳትፎ የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለጸ

58
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 ለአገሪቷ የንግድ መስፋፋትና የኢንዱስትሪ ልማት እድገት የሴቶች ተሳትፎ የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለጸ። ሴቶችም በዘርፉ የነቃ ተሳትፎ እንዳያደርጉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችንም በማስቀረት ረገድ ሰፊ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገልጿል። ምክር ቤቱ  የመጀመሪያ የሆነውን 'ኢትዮ-ቻምበር ውሜንስ ኢን ቢዝነስ' በሚል ርዕስ በንግዱ ዓለም የሴቶችን ተሳትፎ የሚደግፍና የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች የሚመክሩበት ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ አዘጋጅቷል። የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር  መልአኩ እዘዘው እንደተናገሩት፤ "ንግድና ኢንቨስትመንት ለአንድ አገር እድገት ያለው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፤ የሴቶች በዘርፉ መሳተፍ ደግሞ ለበለጠ ስኬት ያደርሳል"። በመሆኑም ምክር ቤቱ የግሉን የንግድ ዘርፍ በማጠናከር በተለይም የሴቶችን አቅም ለማጎልበት ገቢና የስራ እድል የመፍጠር አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ከፌዴራል የስራ እድል ፈጠራና ከምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ጋር እየሰራ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፎረም መዘጋጀቱም በንግዱ ዓለም ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ልምድ እንዲለዋወጡና የቢዝነስ ትስስር እንዲፈጥሩ እንዲሁም በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ዙሪያ እንዲመካከሩ እድል ይጥራል ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሄሩት ዘመነ በበኩላቸው፤ "ሴቶች በኢኮኖሚው ዘርፍ ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዕድል ካልተሰጣቸውና ካልታገዙ የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት አይቻልም" ነው ያሉት። ኢትዮጵያ እያራመደች ያለውን የልማትና የእድገት ጎዳና በተለይም የሁለተኛውን የትራንስፎርሜሽንና እቅድ ግብ ለማሳካት የሴቶች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መጎልበት አለበት ብለዋል። የእናት ባንክ የቦርድ አባል ወይዘሮ ሀና ጥላሁን፤ "ሴቶች በየትኛውም የስራ መስክ ቢሰማሩ ስኬታማ የማይሆኑበት ምንም ነገር የለም፤ በንግዱ ዓለምም ቢሆን የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላሉ ብለዋል"። ነገር ግን ሴቶች  በንግድ  ዘርፍ በሰፊው እንዳይሳተፉ ማነቆ ከሚሆኑባቸው ነገሮች መካከል "በልምድ 'ይህ ስራ የወንዶች' መስሎ የሚታያቸው የማህበረሰቡ ክፍል ስላሉ በድፍረት እንዳይገቡበት ያደርጋቸዋል" ብለዋል። ለሴቶች የተለየ የብድር አገልግሎትና ሴቶች በኢኮኖሚ ብቁ እንዲሆኑ የሚሰራ ተቋም ቢኖር መልካም ነው ያሉት ወይዘሮ ሀና፣ የእናት ባንክም ይህን ዓላማ አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በዘርፉ በሴቶች ዙሪያ የተዘጋጀ የህግ ማዕቀፍና ፖሊሲ ቢኖር ሴቶች በንግዱ ዓለም ተሰማርተው የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡም አክለዋል። ምክር ቤቱም በዚህ ረገድ የተሳካ የሴቶች ተሳትፎን ለማረጋገጥና በኢኮኖሚ እራሳቸውን የቻሉ ብሎም ቁጥራቸው በርከት ያለ የሴት ባለሃብቶችን ለማፍራት የሚያጋጥሙትን ማነቆዎች ለመፍታት በቀጣይነት እንደሚሰራም ገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም