የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት መደሰታቸውን ገለጹ

66
ኢዜአ ታህሳስ 02/2012--- የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት መደሰታቸውን ገለጹ። ከነዋሪዎቹ መካከል የፍቼ ሃገረ ስብከት ጽህፈት ቤት ተጠሪ ቄሲስ ብርሃኑ ወልደ ተንሰኤ እንዳሉት ሰላምና እድገት እውን የሚሆነው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላማዊ አመራጮችን በማሳየት ነው። በተለይ መቻቻልና ለሰላም በጋራ መስራት ለውጤት እንደሚያበቃ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሸልማት ጥሩ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል ። ሽልማቱ እልቂት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ የሃገር ውስጥ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት መንገድ የሚከፍት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሰላሌ ዩኒቨርስቲ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ሴኔሳ ነጋሹ ናቸው ። ሁከት ሃገርን ወደ ባሰ ድህነት የሚከት እንደሆነ ጠቁመው ሰላምን ለማምጣት ትግስትና ይቅር ባይነትን የሚጠይቅ መሆኑን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሸልማት መረዳት እንደሚቻል ገልጸዋል። መምህር አብዮት ቶልቻ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ሸልማት እያንዳንዱ ዜጋ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ልማት መጎልበት የበለጠ የሚያነቃቃ እንደሆነ ተናግረዋል ። በፍቼ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያው አቶ እሸቱ መገርሳ የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ አለም በበጎ ገፅታ ተገንዝቦ እንዲያግዝ ሽልማቱ እድል የሚከፍት በመሆኑ መደሰታቸውን አመልክተዋል። ኢትዮጰያውያን ለሰላምና ፍትህ መስፈን የሚያደርጉትን ጥረት የሚያጠናከር እንደሆነም ጠቁመዋል ። የፍቼ ወጣቶች ማህበር አባል ታሪኩ ውለታው  እንዳለው ችግሮችን ለመፍታት መግባባትና ውይይት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ብቻ ሳይሆን ለውጤት የሚያበቃ እንደሆነ ሽልማቱ ማሳያ ነው። በሽልማቱም መደሰቱን ገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም