ኮሚሽኑ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያየ

83
ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በሃሪቱ የሚነሱ ጥያቄዎች ብዝሃነትን በሚያከብር እና አንድነት በሚያጠናክር መልኩ የሚፈታ ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ መተግበር መጀመሩ ተገለጸ፡፡ ኮሚሽኑ በጉዳዩ ላይ ከክልሎች ጋር የሚያደርገውን ውይይት ትናንት ከቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአሶሳ ጀምሯል፡፡ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዶክተር ጣሰው ገብሬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ኮሚሽኑ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ተግባራዊ የሚያደርገውን ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቷል፡፡ ካለፈው ህዳር ወር 2012 ጀምሮ ወደ ትግበራ መግባቱንም ገልፀዋል፡፡ ስትራቴጂክ እቅዱ አስር ግቦች እና ሶስት የትኩረት መስኮች እንዳሉት ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡ በስትራቴጂክ እቅዱ መሠረት በአስተዳደር ወሰን፣ በማንነት፣ ራስን በራስ በማስተዳደር እና ሌሎችም መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያካሂደው ሃገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት በቅርቡ እንደሚጀመር አመልክተዋል፡፡ ጥናቱ በዋናነት በተመረጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማካኝነት እንደተከናወነ ጠቁመው ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እንደሚያካትት አብራርተዋል፡፡ ከጥናቱ የሚገኘውን ውጤት አፈጻጸም መልክ ለማስያዝ የአስተዳደር ወሰን፣ የማንነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር እና አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብ አፍላቂ ንኡስ ኮሚቴዎች በኮሚሽኑ ስር መዋቀራቸውን አስረድተዋል፡፡ ''ኮሚቴዎቹ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና አባላትን ያቀፉ ናቸው'' ብለዋል፡፡ “ኮሚሽኑ ያለማንም ጣልቃ ገብነት እና ጫና በነጻነት እየሠራ ነው” ሲሉ ያመለከቱት ዶክተር ጣሰው እቅዱ በተቀመጠለት ጊዜ ማጠናቀቅ ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ኮሚሽኑ በተጠቀሰው ጊዜ ስራውን ሲያጠናቀቅ ብዝሃነትን የሚያከብር እና ሃገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የምክር፣ የመፍትሔ እና የውሳኔ ሃሳቦችን ለሃገሪቱ አስፈጻሚ አካል ያቀርባል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ በክልሉ የቆዳ ቀለምንና የህዘብ ቁጥር ማነስን ተከትሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቢቀንሱም አሁንም እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ በክልሉ ህገ-መንግስት በግልጽ በሚቃረንና አስተዳደራዊ ወሰኖችን እውቅና በሚሻማ መልኩ የተለያዩ ዘመቻዎች በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እንደሚተላለፉ አስረድተዋል፡፡ “ይህ ግን በየትኛውም ማህበረሰብ አቋም አይደለም” ያሉት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ “በጥቂት ግለሰቦች ቆስቋሽነት የሚፈጸም ሲሆን ኮሚሽኑ ለመሠል ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥ አምናለሁ” ብለዋል፡፡ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘላለም ጃለታ በበኩላቸው “ለውጡን የማይፈልጉ ጥቂቶች ’አሃዳዊ ስርዓት’ ሊመጣ ነው’” የሚሉት ማደናገሪ እንደሆነ ጠቅሰው ከሚሽኑ ትክክለኛ ስራ በማከናወን እውነታውን ያሳያል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ የኮሚሽኑ አባላት የተለያየ ፖለቲካ ፖርቲ አባላት መሆናቸው፣ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ወይ የሚሉ እና ሌሎች በአመራሮቹ ከተነሱ ጥያቄዎችም ይገኛሉ፡፡ ከኮሚሽኑ አባላት መካከል አቶ የሽዋስ አሰፋ የኮሚሽኑ አባላት የተለያዩ የፖቲካ እና ሌሎችም አመለካከቶች ያላቸው መሆኑ እንደመልካም አጋጣሚ እንጂ ስጋት እንደማይሆን ጠቅሰዋል፡፡ “ፖለቲካ ጊዜያዊ ሃገር ዘላለማዊ ናት” የሚሉት አቶ የሽዋስ “ከኮሚሽኑ አባላት ፖለቲከኞች ቢሆኑም ግጭትን ከሃገሪቱ በዘላቂነት በማስወገድ ሠላማዊ ሃገርን ለማውረስ በእውነት የቆሙ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው “የኮሚሽኑ አባላት ለውጡ የከፈተውን ምህዳር ተጠቅመው የትኛውንም ጉዳይ በውይይት ይፈታሉ” ብለዋል፡፡ “ማንነት ላይ በስፋት የተሠራው አገራዊ አንድነትን አስቷል ”የሚሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሐብታሙ ታዬ ሲሆኑ ይህም “ጽንፈኝነትን በማስፋፋት ሃገሪቱን ለውጥረት ዳርጓታል” ይላሉ፡፡ ከሚሽኑ እነኚህን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው መሰል ገለልተኛ ተቋማትን በማቋቋም በርካታ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ጠቁመው ለተግባዊነቱ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ ኮሚሽኑ በስትራቴጅክ እቅዱ ላይ የሚያደርገው ውይይት በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚቀጥል በዚሁ ወቅት ተገልጸል፡፡ የካቲት 2011 ዓ.ም. የተቋቋመው የህገ-መንግስት፣ ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽን 41 አባላት አሉት፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም