በክልሉ ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከመጤ ተምች መከላከል ተቻለ

61
አዲስ አበባ ሰኔ15/2010 በኦሮሚያ ክልል ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከአሜሪካ መጤ ተምች መከላከል መቻሉን የክልሉ የግብርናና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ ገለፀ። የቢሮው ምክትል ኃላፊና የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሐምዛ መሀመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተምቹ በአሁኑ ወቅት በ15 ዞኖች ውስጥ ባሉ 211 ወረዳዎች ተከስቷል። በዚህም 204 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተ ሲሆን በብዛት በበቆሎ ሰብል ላይ መታየቱንም ነው የገለጹት። እስካሁን ከ45 ሺህ ሊትር በላይ ኬሚካል ወደ ዞኖች ተሰራጭቷል ያሉት አቶ ሐምዛ ከኬሚካሉ በተሻለ አርሶ አደሩ በልማዳዊና በባህላዊ መንገድ የሚያደርጋቸው የተምች ቁጥጥሮች ውጤታማ ናቸው ብለዋል። ተምቹን የመከላከል ስራ በአንዳንድ ዞኖች ውጤታማ ሲሆን በሌሎች ደግሞ የመዘናጋት ሁኔታዎች አሉ ብለዋል። በክልሉ በጅማ፣ ባሌ፣ አርሲ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሀርረጌ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ምስራቅ ወለጋ እና ቄላም ወለጋ ዞኖች ተምቹ በብዛት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች ተምቹን ለመከላከል በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ ቢሆንም ተምቹ ፈጣን በመሆኑ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የምርምር ተቋማት ኀብረተሰቡን ሊያግዙ እንደሚገባም ነው የገለፁት። ባለፈው ዓመት ተምቹ በክልሉ 357 ሺህ ሄክታር ላይ ተከስቶ በተለያዩ ዘዴዎች ለመከላከል ጥረቶች ተደርጎ ከ56 በመቶ በላይ አርሶ አደሩ በራሱ በባህላዊ መልኩ የተከላከለበተና ልምድ የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል። በአግባቡ የመከላከል ስራ ካልተሰራ ተምቹ ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ኃይል ስላለው በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በተወሰኑ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ ከዘነበ ተምቹን ያጠፋል የሚል አመለካከት አለ ይህም ስህተት በመሆኑ በአግባቡ ተምቹን ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ በዚህ ዓመት ተምቹ ከ326 ሺህ በላይ ሄክታር ላይ የተከሰተ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ160 ሺህ በላይ ሄክታር ላይ የተከሰተውን መከላከል መቻሉን የግብርና እና የተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ገልጿል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙት ባለሙያ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ እንዳሉት ከኬሚካል ይልቅ በባህላዊ መንገድ ተምቹን መከላከሉ ውጤታማ በመሆኑ አርሶ አደሩ በተደራጀ መልኩ መስራት አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም