ዶክተር አብይ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸዉ ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ ሰላም የጎለ አስትዋጽኦ ያበረክታል - የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

66

ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸዉ በኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም እንዲጎለበት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

በደሴ ከተማ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሞላ አራጌ እንደገለጹት ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸዉ በኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን ጉልህ ሚና ይጫወታል።

አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለዉን የጥላቻና የመበሻሸቅ እንቅስቃሴ በመቅረፍ ሁሉም በአንድ ኃይል ታሪክ ሰርቶ ከኋላ ቀርነትና ድህነት ለመላቀቅ መነሻሻትን እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

''ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዉስብስብ ወቅት ታግሰዉ ለሰላም፣ ለአንድነትና ለፍቅር ያበረከቱት ጉልህ አስተዋዕጾ ሁላችንንም አኩርቶናል'' ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የሚያርጉት ተነሳሽነትም አበረታች መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ሌላዉ የቧንቧ ዉሃ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሸህ አደም አወል በበኩላቸዉ ዶክተር አብይ አህመድ ለሁለት 10 ዓመታት በአይነ ቁራኛ ይተያዩ የነበሩ የኢትዮጵያና ኤርትራን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር ያደረጉት አስተዋዕጾ ለሌሎች አገራት ምሳሌ መሆን የቻለ ነው፡፡

''በትብብርና በመተጋገዝ የማይወጣ ዳገት አለመኖሩንም በተግባር አሳይተዉናል'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

''ከዚህ በፊት በድህነትና በጦርነት ትታወቅ የነበረችን አገር በአለም የሰላም ተምሳሌት ሆና ስሟ በአላም ሲስተጋባ ከማየት በላይ ምን ደስታ አለ'' ያሉት ሸህ አደም በሽልማቱ ኩራት እንደተሰማቸዉ ገልጸዋል፡፡

''ሽልማቱ የኢትዮጵያ ቀጣይ ተስፋ እንዲለመልም'' አድርጓል ያለዉ ደግሞ የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ዳዉድ አህመድ ነዉ፡፡

እኛ ወጣቶችም ተስፋ ሳንቆርጥ በአንድነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአለም ታሪክ መስራት እንድንችልም አነሳስቶናል ብሏል፡፡

የተጀመረዉ አገራዊ ለዉጥ እንዲቀጥል፣ ሰላም፣ ፍቅርና መቻቻል እንዲጎለብትም አስተዋዕጾዉ የጎላ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ በአለም ተጽኖ መፍጠር እንድትችልና የአለም ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ያለ ስጋት ሀብታቸዉን እንዲያፈሱና ኢንቨስትመንቱ እንዲነቃቃም ያደርጋል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ስም በአለም ጎልቶ እንዲጠራና የህዝቦቿን ታላቅነት በተግባር ስላሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና ይገባቸዋል፤ በስራቸውም ኮርተንባቸዋል ሲል ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም