በሚቀጥሉት 10 ቀናት ዝናብ ሰጭ የባህርና ከባቢ አየር ክስተቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ

129
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 በሚቀጥሉት አስር ቀናት ዝናብ ሰጭ የባህርና ከባቢ የአየር ክስተቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው በትናንት ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ። በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባባቦር፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ ዞኖችና አዲስ አበባ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ ይሆናሉ። እንዲሁም በአማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ የሰሜን ሸዋ፣ በትግራይ ክልል ሁሉም ዞኖች ከመደበኛ ዝናብ ተቀራራቢ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል። በተጨማሪም የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ክልል ዞኖች፣ በደቡብ ክልል የከፋና የቤንች ማጂ ፣ የጉራጌ፣ የሃድያና የወላይታ፣ የሲዳማ ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛው ዝናብ ጋር የተቀራረበና አልፎ አልፎ በጥቂት ቦታዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ። በተጨማሪም ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች በጥቂት ስፍራዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ። ድሬዳዋና ሐረር፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ እንዲሁም አጎራባች የአፋር ዞኖች ዞን3 እና 5 በጥቂት ስፍራዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ የኤጀንሲው ትንበያ ይጠቁማል። ቀሪዎቹ የአገሪቷ አካባቢዎች ግን አልፎ አልፎ ከሚኖራቸው የደመና ሽፋን በስተቀር በአብዛኛው ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ። ከመደበኛው ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ጋር ተያይዞ በአብዛኛው የመኸር አብቃይ አካባቢዎች የማሳ ዝግጅትና ዘር የመዝራት ስራዎች የሚከናወኑበት ወቅት በመሆኑም ለግብርናው ስራ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች ከመጠን በላይ ከፍተኛ የእርጥበት ሁኔታ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህ ሁኔታ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን  ሊፈጥርም ይችላል። ከመጠን በላይ ውሃ ማሳ ላይ በመተኛትም በእርሻ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኤጄንሲው አሳስቧል። በተያያዘም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ እርጥበት እንደሚስተዋልና ይህንንም ተከትሎ የባሮአኮቦ፣ የኦሞጊቤ፣ የተከዜ የላይኛውና የመካከለኛው አዋሽ ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም የላይኛው ዋቢ  ሸበሌና የገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብና ከመደበኛው በላይ የሆነ ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመሬት ሽፋኑ የሳሳ በመሆኑ አልፎ አልፎ በሚከሰተው ከባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ሊያስከትል እንደሚችል ትንበያው ጠቁሞ ህብረተሰቡ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኤጄንሲው አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም