የኢትዮጵያን ተምሳሌታዊ ድሎች በዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ማስፈን ሂደት መድገም ይገባል...ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም

85
ኢዜአ፤ታህሳስ 2/2012 የኢትዮጵያን ተምሳሌታዊ ድሎች በዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ማስፈን ሂደት መድገም እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም ገልጸዋል።
ወደ ሰላምና ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ የምናሳካው በእውቀትና በጥበብ ብቻ ነው መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
ፕሮፌሰር ሂሩት የአድዋን፣ የአበበ ቢቂላን የማራቶን ድል፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የሰላም ኖቤል ሽልማት፣ የጥምቀትን በዩኔስኮ መመዝገብ በአኩሪና አስተማሪ ታሪክነት ጠቅሰዋል።
 
ከዚህ ቀደም እና አሁን እየተመዘገቡ ያሉ ድሎችንም ለማስቀጠል በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትውልድን መፍጠር እንደሚገባ መጥቀሳቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
 
ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የሚያስፈልጋትን የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ዩኒቨርስቲዎች ከሁከትና ግርግር የፀዱ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
 
“ተምሳሌታዊና አንገታችንን ቀና አድርገን ኢትዮጵያዊነታችንን እንድንመሰክር ያደረጉንን ድሎች በዩኒቨርስቲዎቻችን ሰላም የማስፈን ሂደትም ልንደግማቸው ይገባል” ነው ያሉት።
 
ዩኒቨርስቲዎች የሰላም ቤት፣ የእውቀት ማዕድ የሚቆረስባቸው፣ የምርምርና ፈጠራ ማዕከላት ብቻ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ሚኒስትሯ።
 
አጥፊዎችን በማጋለጥ፣ ከጥፋተኞች ጎን ባለመቆምና ባለመሸሸግ በየዩኒቨርስቲው ያሉ ሀገራቸውን ወደፊት አንድ እርምጃ የሚያራምዱ ትውልዶችን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ሁሉም እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
 
“ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል፡፡ ይሔንን የተማረ ኃይል ለማፍራት ደግሞ ዩኒቨርስቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት ብቻ የሚከናወንባቸው፤ ከማንኛውም አይነት ሁከትና ግርግር የፀዱ ሊሆኑ ይገባል፡፡” ብለዋል
 
የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላም አስጠብቆ፣ የተማሪዎችን ደህንነት አስከብሮ ለመቀጠል የሁሉም አካላት የተግባር ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት”
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም