በአየር ንብረት መዛባት አፍሪካ ችግሮች እየገጠሟት ነው  

45

ኢዜአ፤ ታህሳስ2/2019 ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ  በአፍሪካ አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡

መሻሻሎች ቢኖሩም እስካሁን ድረስ በአፍሪካ የተገኘው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች በቀላሉ የተጋለጠ በመሆኑ አገራዊ ግቦችን ለማሳካትና አጠቃላይ የ2063 አጀንዳዎችና ዓለም አቀፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማስቀጠል እንቅፋት እየፈጠረ እንዳለ አፍሪካ ህብረት ትላንት ያወጣው መግለጫ ያስረዳል፡፡

ባለፉት 20 አመታት ውስጥ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በተከሰተው በሽታ  በማላዊ፣ሞዛምቢክና ዚምባብዌ ከ 1 ሺህ ሰዎች በላይ መሞታቸው በቅርብ የወጣው የአፍሪካ ሃገራት መረጃ እንደሚያሳይ ተጠቅሷል።

በሞዛምቢክና በኮሞሮስ በድጋሚ ባጋጠመው በአውሎ ንፋስ የመመታት አደጋ ወደ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ መድረሱን የፓን አፍሪካ ቡድን አስረድቷል፡፡

በቅርቡ የዓለም ባንክ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ በርካታ የአፍሪካ አገራት አመታዊ እድገት 4.5 በመቶ ቢያሳይም የውሃ ና የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ስጋት መደቀኑ ተገልጿል፡፡

ህብረቱ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተኮር አጀንዳዎች የፓሪስ ስምምነትን፣ ዘላቂ የልማት ግቦችና አዲሱ የከተማ አጀንዳ የመተግበሩ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

የአየር ሁኔታ በተመለከተ የተዘጋጁት ፖሊሲና ስትራተጂዎች በተግባር ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ለውጥ መታየት አለበት የተባለ ሲሆን፤ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት  ሀብቶችን በማሰባሰብ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም ተገልጿል።

በተመሳሳይ በአፍሪካ ሆነ በአለም እየተስተዋለ ያለውን የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮችን ለማስቀረት የአለም ማህበረ ሰብ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ መቅረቡን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም