በጋምቤላ ክልል የምርት ግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቀቀምን በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

65
ጋምቤላ ሰኔ 15/2010 በጋምቤላ ክልል በዘንደሮው የመኸር እርሻ የምርት ግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቀቀምን በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ በተያዘው በመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው 114 ሺህ ሄከታር መሬት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በተለያዩ የሰብል ዘር መሸፈኑንም ቢሮው ገልጿል። የቢሮው ኃላፊ ዶክትር ሎው ኡቡፕ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የመኸር እርሻ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የግብርና መካናይዜሽንና በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂ አጠቀቀምን በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው። በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው መሬት 70 ከመቶ የሚሆነውን በመስመር ለመዝራት አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ የእርሻ ትራክተር በመጠቀም ሰፋት ያለው መሬት እንዲያለማ በባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል። በዘንደሮው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው114 ሺህ ሄክታር መሬት እስከ ሰኔ መጀመሪያ ሳምንት ባለው ጊዜ ከግማሽ በላይ የሚሆነው መሬት ቀድመው በሚዘሩ የበቆሎ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ ፣ የጓሮ አትክልትና በሌሎች የሰብል ዘር ዓይነቶች መሸፈኑን ገልጸዋል። እየለማ ያለው መሬት ከቀዳሚው ዓመት በ41ሺህ ሄክታር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል። በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው ከዚሁ መሬት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ አልፎ አልፎ ተከስቶ የነበረው የአሜረካ መጤ ተምች በጸረ-ተባይ ኬሚካል እርጭትና በእጅ ለቀማ ብዙ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ሰር መዋሉን ጠቁመዋል። የአበቦ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ቱል ኡጀሉ እንደሚሉት በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለአርሶ አደሩ የስልጠና፣ ኤክስቴንሽና የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ ካለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ ወደ ልማቱ እንዲገባ ተደረጓል ብለዋል። በወረዳው ተከስቶ የነበረውን የአሜሪካ መጤ ተምች በባለሙያዎች በተደረገው የክትትልና ድጋፍ ስራ ብዙ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል። በአበቦ ወረዳ የቾቦ ኪር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኡሞድ ቻም በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው ዓመት የግብርና ባለሙያዎች የምርጥ ዘር አቅርቦትና ማሳቸውን በመስምር እንዲዘሩ ጭምር ድጋፍ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል። በዘንድው ዓመት የግብርና ባለሙያዎች ባደረጉላቸው ድጋፍ በትራክተር በመታገዝ የተሻለ መሬት ማልማታቸውንና የሰብሉም ቡቃያ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሌላው የቾቦ ኪር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አሪያት ኡሞደ ናቸው። የጋምቤላ ወረዳ የፊንኬዎ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኡቶው ኡጆሆ በበኩላቸው በዘንደሮው ዓመት በባለሙያዎች ከተደረገላቸው ድጋፍና ክትትል በተጨማሪ በቂ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዳገኙ ተናግረዋል። በክልሉ ባለፈው የመኸር እርሻ ከ73 ሺህ በላይ መሬት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደተሰበሰበ ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም