በማዕከላዊ ጎንደር የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ማገዙ ተገለጸ

158
ጎንደር ግንቦት 2/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡና ከክፍል እንዳይቀሩ ማገዙ ተገለጸ፡፡ በዞኑ ከ55ሺ በላይ የቅድመና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡ በወገራ ወረዳ የብራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕስ መምህር አቶ ሀብቱ ገበየሁ ለኢዜአ እንዳሉት የምገባ ፕሮግራሙ በመማር ማስተማር ስራው የተማሪዎችን መቅረትና ማቋረጥ በማስቀረት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው። የምገባ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በቅድመ መደበኛ ትምህርት ፕሮግራም ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ 75 ህጻናቶች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ ችለዋል፡፡ "በአንደኛ ደረጃ ትምህርትም በአንድ ክፍል ውስጥ ከትምህርት ገበታ ይቀሩ የነበሩ 20 ተማሪዎች አሁን ላይ የሚቀሩት ከ2 ተማሪዎች አይበልጡም "ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ ለምግባ ፕሮግራሙ ባደረገው የ12ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ 6 ምግብ አዘጋጆች ተቀጥረው በየዕለቱ ተማሪዎቹን እየመገቡ ናቸው፡፡ እየተገባደደ ባለው የትምህርት ዘመን በ26 ትምህርት ቤቶች ከ14ሺ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ የወገራ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ ሙላው ናቸው፡፡ ለምገባ ፕሮግራሙ በመንግስት ከ1ሺህ ኩንታል በላይ የዳቦ ዱቄት መቅረቡን ጠቁመው፤" ህብረተሰቡ ለፕሮግራሙ መሳካት የገንዝብ ፣የጉልበትና የቁሳቁስ ድጋፍ እያበረከተ ነው" ብለዋል፡፡ የምገባ ፕሮግራሙ መጀመር ቀደም ሲል በተማሪዎች ይስተዋል የነበረው ትምህርታቸውን የማቆራረጥ ባህሪ ችግር አሁን እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል። በዞኑ ትምህርት መመሪያ የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪ አቶ በየነ መረሳ  በበኩላቸው  " ከመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በዞኑ 141 የቅድመ እና የመጀመሪያ  ደረጃ ትምህርት ቤቶች 55 ሺህ ተማሪዎች በምገባ ፕሮግራሙ እየተጠቀሙ ነው"  ብለዋል፡፡ የምገባ ፕሮግራሙ የተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ድርቅ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸውና የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ተጋላጭ አካባቢዎች እንደሆኑም ጠቁመዋል። ቡድን መሪው እንዳመለከቱት ምስራቅ በለሳ ፣ወገራና ኪንፋዝ በገላ በተባሉት የዞኑ ወረዳዎች ለተጀመረው የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም የሚውል መንግስት 4ሺህ 390 ኩንታል የዳቦ ዱቄት አቅርቧል፡፡ የአልሚ ምግብ ይዘት ያለው የዳቦ ዱቄቱ ለተማሪዎቹ በየዕለቱ በትምህርት ሰዓት በዳቦ መልክ ተዘጋጅቶ ለቁርስ  እየቀረበላቸው ነው፡፡ ህብረተሰቡ የምገባ ፕሮግራሙን በመደገፍ ምግብ ለሚያዘጋጁ እንዲሁም የማገዶ እንጨትና ውሃ ለሚያቀርቡ ሰራተኞች የጉልበት ዋጋ ክፍያ በመሸፈን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። "የምገባ ፕሮግራሙ መካሄድ በወረዳዎቹ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ይስተዋል የነበረውን የተማሪዎች ትምህርት የማቋረጥና ከትምህርት ገበታ መቅረትን በመቀነስ በኩል አስተዋጽኦ አድርጓል " ብለዋል ቡድን መሪው፡፡ "መንግስት የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም እንዲጀመር በማድረጉ ወላጆች ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል "ያሉት ደግሞ በወገራ ወረዳ የብራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ቄስ አሰፋ ፉላ ናቸው፡፡ " እኔ ለራሴ በወር 12 ብር መዋጮ እያዋጣሁ እየደገፍኩ ነው "ያሉት ቄስ አሰፋ የሚዘጋጀው ዳቦ የአልሚ ምግብ ይዘት ያለው በመሆኑ ለተማሪዎች የአእምሮ እድገትና ጤና በጎ እንደሆነ መገንዘባቸውንም ተናግረዋል፡፡ ዞኑ ትምህርት መምሪያ  እንዳመለከተው ምገባው እስከ ትምህርት ማብቂያ ሰኔ ወር ድረስ ይዘልቃል፤  ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያም መንግስት 13 ሚሊዮን ብር በላይ መድቧል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም