ግንባታው የተጀመረው የኮምቦልቻ ዘመናዊ መነሃሪያ በተያዘለት ጊዜ አልተጠናቀቀም

63
ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 በኮምበልቻ ከተማ ግንባታው የተጀመረው ዘመናዊ መነሃሪያ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ለችግር መጋለጣቸውን አሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች ገለጹ። የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ የመነሃሪያ ግባታው የተጓተተው በተቋራጩ አቅም ዉስንነት ምክንያት መሆኑን አመልክቷል። በኮምቦልቻ ከተማ የ02 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ፉዓድ ይመር እዳለው ከኮምቦልቻ ደሴ በትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ስራ መሰማራቱን አስታውቋል። ይሁን እንጅ ከአራት ዓመት በፊት የድሮዉን መነሃሪያ በዘመናዊ መንገድ ለማልማት የተጀመረው ግንባታ እስካሁን ባለመጠናቀቁ በስራቸው ላይ እንቅፋት በመፍጠር ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡ አሁን እየተጠቀሙበት ያለው ጊዜያዊ መነሃያ  አጥርና በቂ ጥበቃ የሌለው በመሆኑ የቆሻሻ መጣያ በመሆን  ለሽታ ከመጋለጣችንም ባለፈ የተሸከርከሪዎች እቃ እየተሰረቀ ለኪሰራ እየተዳረጉ እንደሚገኙ አስረድቷል። ''በተደጋጋሚ የሚደርስብንን ችግር ለሚመለከተዉ አካል ብናሳዉቅም መልስ በማጣታችን ሌላ ቦታ ገንዘብ እየከፈልን መኪና ለማሳደር በመገደዳችን ለተጨማሪ ወጭ እየተዳረግን ነው'' ብሏል፡፡ ሌላዋ የ08 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት ዮሐንስ እንደገለጹት ''ጊዜያዊ መነሃሪየው ከጥበቱ ባለፈ  ጭቃውና ቆሻሻው እንደልባችን እንዳንገለገል አድርጎናል'' ብለዋል፡፡ በጊዜያዊ መነሃሪያው የጸጥታ ሃይል ባለመኖሩም ተገልጋዩ በተደጋጋሚ ለተለያየ ችግር ሲጋለጥ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮንስተራክሽን ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ መሃመድ አሚን የሱፍ በበኩላቸዉ የመነሃሪያ ግንባታው ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ቢታቀድም በተቋራጩ አቅም ውሱንነትና የጥራት ችግር ምክንትያ መጓተቱን ገልጸዋል፡፡ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠዉም ማስተካከል ባለመቻሉ ዉሉ እንዲቋረጥ በማድረግ አሁን ላይ ከስ እንዲሚሰረተበት ተደርጎ ጉዳዩ በህግ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የህብረተሰቡ ጥያቄ ትክክል ነዉ ያሉት ስራ አስካሄጁ በየደረጃዉ በተደረገዉ ዉይይት መሰረት አዲስ ጨረታ ወጥቶ ሌላ ተቋራጭ በ100 ሚሊዮን ብር ለማስገባት ስራው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ''በዘመናዊ መንገድ የሚገነበባውን መነሃሪያ ጥራቱን ጠብቆ በሁለት ዓመት እንዲያጠናቅቅም ክትትልና ድጋፍ እናደርጋለን'' ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ አሁን እየተስተዋለ ያለውን ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታትም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ህብረተቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለመቅረ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም