አቶ ገዱ ከአሜሪካው አቻቸው ማይክ ፖምፒዮ ጋር ተወያዩ

62

ኢዜአ፤ ታህሳስ 2/2012 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአሜሪካው አቻቸው ማይክ ፖምፒዮ ጋር በአገራቱ የሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዋሽንግተን ተወያዩ፡፡

አቶ ገዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ እያከናወነችው ባለው ለውጥና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መስፈን አሜሪካ እያደረገች ላለው ድጋፍ ኢትዮጵያ ታላቅ ግምት ትሰጣለች።

በኢኮኖሚ መስክ ለሚደረገው አገር በቀል የምጣኔ ሃብት የለውጥ ጉዞ እና በተቋማት ግንባታ ረገድ አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ውይይት በውጤት እንዲቋጭ እና በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ረገድ ጥረቷን እንደምትገፋበት የገለጹት አቶ ገዱ፤ ለዚህ ስኬት የአሜሪካ አጋርነት ወሳኝ እንደሆነም አስረድተዋል።

ህዳሴ ግድቡ ጋር ኢትዮጵያ የማንንም ጥቅም ለመጉዳት ሳይሆን የህዝቦቿን የዘመናት የልማት ጥያቄ ለመመለስ የምትገነባው አገራዊ ፕሮጀክት እንደሆነም ገልጸውላቸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማታቸውን በመቀበላቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፤ ይህም ለጀመሩት የለውጥ ጉዞ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እንደምትደግፍ፤ በተለይም የአሜሪካ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ግፊት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

ለዚህም ስኬት የተቋማት የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥና የኢንቨስትመንት ስራ ምቹነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ከቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አኳያ በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጉዳይ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መስተጋብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ልዩነታቸውን በውይይት ብቻ እንዲፈቱ የአገራቸው ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ገልጸው ለዚህም ድጋፏ ይቀጥላል ማለታቸውን  ከውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም