ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቷ ያስጀመሩትን ለውጥና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ልናግዛቸው ይገባል ---የመዲናዋ ነዋሪዎች

81

ታህሳስ 01/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገሪቷ ያስጀመሩትን ለውጥና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ልናግዛቸው ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ህዝቦች ስም የተቀበሉት የሰላም ኖቤል እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በኖርዌይ ርዕሰ መዲና ኦስሎ ተገኝተው የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን መቀበላቸው ይታወሳል።

ሽልማቱን በማስመልከትም ኢዜአ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ሽልማቱ በቀጣይ ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ዘርፈ ብዙ  እንቅስቃሴዎች ላቅ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አንስተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ራሃዋ መሃመድ እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ሰላምን መፈለጋቸው ህዝቡም የሚመኘው ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ዜጋ ሊያግዛቸው ይገባል ብለዋለ።

አቶ መንግስቱ መኮንን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስጀመሩት ዘርፈ ብዙ ለውጥ ሊደገፍና ሁሉም ዜጋ ሊገነዘበው የሚገባው መሆኑን አንስተው ለወደፊቱም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚኖረው ሚና ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ዘንድ የነጻነት ምልክት አገር እንደሆነች የምትታወቅ በመሆኑም ሽልማቱ ኢትዮጵያውያንን ከማነሳሳት አልፎ ለአፍሪካዊያንም ጭምር መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ሲሉም አክለዋል።

ወጣት አብይ አያሌው በሰጠው አስተያየት ደግሞ የዶክተር አብይ ሽልማት ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ዘርፍ ስኬታማ መሆን የሚችሉ እንደሆኑ ከማሳየቱም በላይ አፍሪካዊያን መሪዎች ከዚህ መማር እንዳለባቸው ማሳያም ነው ብሏል።

አቶ መስፍን ጸጋዬም በሰጡት ሃሳብ ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም ጉዳዮች ላይ በሰሩት ትልቅ ስራ የተበረከተላቸው እንደመሆኑ መጠን ከዚህ በኋላም ስለ ሰላም ለሚሰሩት ትልቅ ተግባራት መነመሳሳትን ይፍጥርላቸዋል ብለዋል።

በቀጣይም አገሪቷ ልትደርስበት ካቀደቻቸው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና ዘርፈ ብዙ ለውጦች ልትደርስ የምትችለው ሰላሟ የተረጋገጠ አገር ስትሆን ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ በሰላም ጉዳይ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመት የዘለቀው አለመግባባት በሰላም እንዲቋጭ ተነሳሽነት ወስደው በመስራታቸው፣ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ባበረከቱት አስተዋጽኦ እና በአገር ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በማድረጋቸው የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ እንደሆኑ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም