የንግዱ ማህበረሰብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እሰራለሁ - የአዲስ አበባ የነጋዴዎች ፎረም

74
ኤዜአ ታህሳስ 1/2012 በከተማዋ የሚገኙ ነጋዴዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሰራ የአዲስ አበባ የነጋዴዎች ፎረም ገለፀ። በአዲስ አበባ የነጋዴዎች ፎረምን ለመምራት የተመረጡ አዲስ ስራ አስፈፃሚዎች ዛሬ ከነጋዴው ጋር ትውውቅ አድርገዋል። ስራ አስፈፃሚው ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን  ከእነዚህም ወይዘሮ ዘሃራ መሐመድ ፕሬዝደንት፣ አቶ ውጅራ ይብጌታ ምክትል ፕሬዝደንት፣ ቴድሮስ ተሾመ ፀሃፊ ሆነው ተመርጠዋል። በትውውቁ ላይ የተገኙት የከተማዋ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ  ሃላፊ አማካሪ አቶ መከታ አዳፍሬ እንደተናገሩት  "ነጋዴዎች ጠንካራ አደረጃጀት መመስረታቸው መብታቸውንና ግዴታቸውን ለማወቅ ያግዛቸዋል"። ይህ አደረጃጀት ነጋዴዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በተደራጀ መንገድ እንዲያቀርቡ፤ በንግዱ ዘርፍ የሚወጡ ህጎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እንዲሁም የመንግስት አሰራር ወደ ተሻለ ደረጃ አድጎ ችግር ፈቺ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል። ነጋዴዎችም  በህጋዊ መንገድ በመደራጀት የነቃ ተሳትፎ በማድረግና  የተሻለ ስራ በመስራት እራሳቸውንና ማህበረሰቡን  ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባቸውም  ተናግረዋል። የፎረሙ ፕሬዝደንት ወይዘሮ ዘሃራ መሐመድ  በበኩላቸው "በንግዱ ማህበረሰብ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ከሚመለከተው አካላት ጋራ በትብብር እንደሚሰሩ ገልፀዋል። ነጋዴው የግብርና ታክስ ህጎች ሲወጡ ተሳትፎ እንዲያደርግ፣ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ህጋዊ መስመር እንዲይዙና ለህጋዊ ነጋዴዎች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር  የማድረግ ስራ እንደሚሰሩም ወይዘሮ ዘሃራ ተናግረዋል። ወይዘሮ ዘሃራ  አክለውም በየደረጃው ያለውን መዋቅር በተገቢው መንገድ በማደራጀት ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን በማስወገድና የተሻለ አሰራር በመዘርጋት ከዘርፉ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጣቸው እንደሚሰሩም ገልፀዋል። የነጋዴዎች ፎረሙ እንቅስቃሴ በንግዱ ማህበረሰብና በመንግስት መካከል መልካም ግንኙነት በማስፈን  የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሆነም ጠቅሰዋል። የንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ እንዲያገኝ ፣ መብቱን እንዲጠይቅ ፣ ግዴታውን እንዲወጣ ፣በአቋራጭ ለማደግ ከሚያደርገው አሉታዊ ተግባር እንዲቆጠብ ለማድረግ በየጊዜው የምክክር መድረክ እንደሚካሄድም ገልፀዋል። ፎረሙ 2003 ዓ.ም ተመስርቶ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቢቆይም ፤ ባለፉት አመታት በስራው ላይ የአሰራር ክፍተት በመታየቱ አዳዲስ የስራ አሰፈፃሚዎች እንዲመርጥ መደረጉም ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም