በአገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማነት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የጉጅ ዞን ነዎሪዎች ገለፁ

1281

ነገሌ ሰኔ 15/2010 በአገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማነት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የጉጅ ዞን ነዎሪዎች ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ ቂም፣ ጥላቻና በቀል እንዲቀር ያስተላለፉት መልእክት አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያስችል አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል፡፡

በዞኑ የአረቀ ከተማ ነዋሪ አቶ ከረዩ አዶላ እንደሉት ቅሬታዎችንና አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት አገራዊ አንድነትን ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደገፍና የሚበረታታ ነው።

“ሰሞኑን በደቡብ ክልል ከባህላችን ባፈነገጠ መልኩ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እራሳችንንና ሀገራችንን የሚጎዳ አሳፋሪ ተግባር ነው” ብለዋል፡፡

አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የነበረው ባህላዊ ልምድ ተጠናክሮ እንዲቆይ በተለይም የሃገር ሸማግሌዎች ወጣቱን የማስተማርና የማሳመን ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት በማካሄድ ላይ ላሉት የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማነት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጅ ናቸው፡፡

የነገሌ ከተማ 03 ቀበሌ ነዋሪ ዋና ሳጅን ለገሰ ናደው በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማው ንግግር ቂም በቀልና ጥላቻን በማስቀረት እርስ በእርስ እንድንከባበር፣ እንድንደማመጥና እንድንቻቻል የሚያደርግ የሰላም ጥሪ በመሆኑ እንደሚደግፉት ገልፀዋል፡፡

በሀገሪቱ ለዘመናት የኖረው የመቻቻል፣ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህላዊ እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አዲሱን ትውልድ ማስተማርና ማስረዳት ይገባልብለዋል፡፡

ህዝብን ከሕዝብ በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የአንድ አንድ ወገኖች የጥፋት መንገድ እንዲቆም ከማስተማር ጉን ለጉን ህግ የማስከበር ስራቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡

የሰላምና የልማት ሰራ ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ በተለይ ወጣቶች ከሁከትና ብጥብጥ ራሳቸውን በማራቅ የመልካም ስነ ምግባር ተገዢ መሆን እንዳለባቸው የገለፁት ደግሞ የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ወልደሰንበት ናቸው።