ሽልማቱ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለተጨማሪ ድል ያነሳሳል---የአፋር ክልላዊ መንግሰት

67

ኢዜአ ታህሳስ 01/2012 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቪል ሽልማት ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለተጨማሪ ድል እንዲነሳሱ የሚያደርግ መሆኑን የአፋር ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ  ኃላፊ አቶ አህመድ ከሎይታ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያዊያን  አብሮነትና ወንድማማችነትን በማጠናከር  ሀገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው።

በቀጠናው ሀገራት የሰላምና አብሮ በጋራ ለማደግ እንቅፋት ሆነው  ከነበሩ የጠላትነትና የጥርጥሬ ስሜቶች ወጥተው  በመደመር እሳቤ ወደ መተማመን መንፈስ እንዲቀየር የመሪነት ሚናቸውን ተጫውተዋል።

በተለይም በኢትዮጵየና ኤርትራ መካከል ለዘመናት የነበረውን የጦርነት ስጋትና የጠላትነት መንፈስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲቀየር ያበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ በታሪክ ሁሌም ሲታወስ የሚኖር በጎ ተግባር እንደሆነ አቶ አህመድ ገልጸዋል።

ለዚህ ስኬታቸውም  ሁሉም  ኢትዮጵያዊያን የራሳቸው  አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲሁም ሰላም ወዳድነታቸው በአርአያነት የሚታይ ነው።

ኃላፊው እንዳስረዱት  የሰላም ኖቤል ሽልማቱ በጠንካራና በሳል አመራር ሰጪነታቸው  ያስለመዘገቡት አንጻባራቂና ታሪካዊ ድል በመሆኑም ይገባቸዋል።

ሽልማቱን እሳቸው  ቢቀበሉትም ድሉና ክብሩ  የመላው  ሀገርና ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊያን  ጭምር በመሆኑ አንድነታችንን በማጠናከር ለተጨማሪ ድል ያነሳሳል።

በሀገር ውስጥና በቀጠናው  የጀመሩትም የሰላም እሴት ግንባታና አብሮነት እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፍጥርም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሽልማቱ አሸናፊ በመሆናቸው  የክልሉ መንግስትና ህዝብ  የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውንም  የኮሙዩኔኬሽን ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም