በትራፊክ አደጋ 2 ሰዎች ሲሞቱ በ17 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደረሰ

73
ኢዜአ ታህሳስ 01/2012 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከማይጨው ከተማ ወደ ነቅሰገ ሲጓዝ የነበረው መኪና ተገልብጦ ሁለት ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ በ17 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ ፖሊስ ገለፀ። በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥርና አጣሪ ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር አብረሃ ወረደ እንደገለፁት  19 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ የተገለበጠው ነቅሰገ ከተማ መግቢያ አካባቢ ነው ። ትናንት ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በደረሰው አደጋ 2 ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ ሾፌሩን ጨምሮ በ17 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ኮማንደሩ ተናግረዋል ። ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 17 ሰዎች በማይጨው ሆስፒታልና በማይጨው ጤና ጣቢያ በህክምና ላይ ይገኛሉ ተብሏል ። የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ትግ 06605 የሆነው ሚኒባስ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ 11 ሰዎች መጫን ሲገባው ትርፍ ጭኖ በመጓዝ ላይ እንዳለ መገልበጡን ገልፀዋል ። የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ ነው ያሉት ኮማንደሩ የትራፊክ አደጋ በየጊዜው እየጨመረ የበርካታ ወገኖች ህይወት እየቀጠፈና የአገርና የህዝብ ንብረት እያወደመ በመሆኑ አሽርካሪዎች በጥንቃቄ እንዲጓዙ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም