የስነ-ምግባር እሴቶች መሸርሸር ለሙስና መስፋፋት መንስኤ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

106

ኢዜአ ህዳር 30/2012 "ከአባቶቻችን የወረስናቸው የስነ-ምግባር እሴቶች መሸርሸር ለሙስና መስፋፋት መንስኤ እየሆነ መጥቷል" ሲሉ የአማራ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ገለጹ።

"መልካም ስነ-ምግባርን በመገንባት፣ ሙስናን ለመታገል ዘላቂ ሰላምና ልማትን እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ሀሳብ  የፀረ-ሙስና ቀን ዛሬ በክልል ደረጃ  በፓናል ውይይት ተከብሯል።

በዚህ ወቅት ኮሚሽነር ዝጋለ ገበየሁ እንዳሉት ሀገራዊ ለውጡ ተከትሎ በተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ምክንያት ሙስና እንደገና እያቆጠቆጠ ይገኛል።

ሙስና እያቆጠቆጠ ከሚገኝባቸው ዘርፎች ውስጥም የገጠር መሬት፣ የበከተማ ቦታ፣ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ፣ በልማት ድርጅቶች በሚናወኑ ተግባራት እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል።

ይህም  የነበሩ መልካም የስነ-ምግባር እሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች እየተሸረሸሩ መምጣት ለሙስና መስፋፋት አይነተኛ መንስኤ  እንደሆነም ተናግረዋል።

የከፋ ችግር ከማስከተሉ በፊት መከላከል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዓሉን  ሲከበር ሙስና በሃገርና በህዝብ ላይ  ያደረሰውን ችግር ሁሉም ተረድቶ ለፀረ ሙስና ትግሉ የድርሻውን እንዲወጣ ለማነሳሳት መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በኮሚሽኑ የስነምግባር ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር በአቶ ሰይድ መሀመድ በበኩላቸው ሙስናን ከመከሰቱ በፊት ከምንጩ መከላከል ካልተቻለ  ለወንጀል መስፋፋትና ለመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት እንደሚሆን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት በሀገሪቱ  ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት አስር ዓመታት በተፈጸመ ሙስና 11 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመዝበሩን  የተደረጉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

በክልሉ ያለእጅ መንሻ የሚሰጥ መንግስታዊ አገልግሎቶች አለመኖሩን ህዝቡ በምሬት እያነሳ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት የህግ ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ ናቸው።

ችግሩን ለመከላከል የተቋቋመውን ክልላዊ የፀረ-ሙስና ጥምረት በማጠናከርና ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ይርሳው ታምሬ በበኩላቸው "ሙስናን የሚፀየፍና በስነምግባሩ የተሟላ ትውልድ ለመፍጠር በሙስና መንስኤዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ልንሰራ ይገባል " ብለዋል።

ፓስተር አበበ የኋላሸት በሰጡት አስተያየት  በየደረጃው የመፈጸም ሙስናን ለመከላከል የኃይማኖት አባቶች ትኩረት ሰጥተው ተከታዮቻቸውን ማስተማር እንደሚነርባቸው ገልጸዋል።

እርሳቸውም እንደ ኃይማኖት አባት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የፀረ ሙስና ቀንም ከህዳር 23 እስከ ህዳር 30/2012 ዓ.ም ድረስ በጥያቄና መልስ፣ በስፖርታዊ ውድድሮችና በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም