በፍጥነት ማሽከርከር የተነሳ የሚከሰት የትራፊክ አደጋ አስከፊ ጉዳት ስለሚያደርስ አሽከሪካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

195
ህዳር 30/2012 ከተፈቀደው በላይ በፍጥነት ማሽከርከር የተነሳ የሚከሰት የትራፊክ አደጋ አስከፊ ጉዳት ስለሚያደርስ አሽከሪካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠየቀ። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በሦስት ከአዲስ አበባ  መውጫ መንገዶች ለአሽከርካሪዎች የግንዛቤ መፍጠር ስራ አከናውኗል። በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ገዳይ ከሚባሉት አደጋዎች የትራፊክ አደጋ በቀዳሚነት ከመጠቀሱም በላይ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። ችግሩን ለመቀነስ የተለያዩ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች በተለያዩ የባለድርሻ አካላት እየተከናወነ ይገኛል። የትራፊክ አደጋ መከሰት ዋና ዋና መንስኤዎችም ከተፈቀደው በላይ በፍጥነት ማሽከርከር፣ አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከርና ቴክኒካል ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ባለስልጣኑ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ መውጫ የፈጣን መንገድ መግቢያ ላይ ለአሽከረካሪዎች መልክት አስተላልፏል። በዚህ ቦታ ላይ አሽከረካሪዎችን እያስተናበሩ ያገኘናቸው የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ትራፊክ አስተባባሪ ኢንስፔክተር አበበ በቀለ እንደገለጹት፤ የትራፊክ አደጋ መከሰት ዋናው መንስኤ አሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው ወሰን በላይ ማሽከርከር ነው። ከመጠን ያለፈ ፍጥነት በቀላሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ገልጸዋል። በከፍተኛ ፍጥነት የሚከሰት የትራፊክ አደጋ ከከፍተኛ የአካል ጉዳት እስከ ሞት የሚያደርስና አምራች ሀይሉን ስለሚጎዳ የቤተሰብ ህይወትን አደጋ ላይ እንደሚጥል አስገንዝበዋል። ''ያለ በቂ እረፍት ለረጅም ሰዓት ማሽከርከርና የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ አለማድረግ ለአደጋ ያጋልጣል'' ብለዋል። በመሆኑም ግንዛቤ በመፍጠር አሽከርካሪዎች ፍጥነትን በመቀነስና የቴክኒክ ብቃትን በማረጋገጥ እንዲሁም ለረጅም ሰዓት ባለማሽከርከር የትራፊክ አደጋን መቀነስ ተገቢ እንደሆነ ኢንስፔክተር አበበ አስረድተዋል። ለ28 ዓመታት ሲያሽከረክሩ ምንም አደጋ ያላደረሱት አሽከርካሪ ያሬድ ስዩም በሰጡት አስተያየት የትራፊክ አደጋን መከላከል የቻሉት የመኪናውን ደህንነት የፍሬን፣ የጎማ፣ የዘይትና መሰል የቴክኒክ ጉዳዮችን አረጋግጠው መኪና የሚያሽከረክሩ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል። ለትራፊክ አደጋ ዋናው መንስኤ የመንገድ ደህንነት ጠቋሚዎች በአግባቡ ሥራ ላይ ባለመዋላቸው እንደሆነ የጠቆሙት ሌላው አሽከርካሪ አቶ ቴዎድሮስ፤ የመንገድ ደህንነትን የሚጠቁሙ ምልክቶች ማበጀት እንደሚገባ ተናግረዋል። ''አሽከርካሪው ፍጥነቱን በመቀነስ በማስተዋልና በጥንቃቄ መንዳት ያስፈልጋል'' ብለዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየው አየለ በበኩላቸው እየተከሰተ ያለውን ከፍተኛ ትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በሦስት ዋና ዋና ከአዲስ አበባ ደብረዘይት፣ ዓለምገናና ደብረድርሃን መውጫ በሮች መከናወናቸውን ተናግረዋል። ባለስልጣኑ ከሚያከናውናቸው የመንገድ ግንባታ ስራዎች ጎን ለጎን የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚያከናውን አመልክተዋል። የግንዛቤ መስጨበጫ ስራው የመንገድ ደህንነት ህጎችን በማስከበርና በማስጠበቅ  የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል። በመሆኑም የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ሁሉም የባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ''በተለይም አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህጉን በማክበር ፍጥነትን በመቀነስ ደህንነታቸው ተጠብቆ ከሚፈልጉት ቦታ እንዲደርሱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል'' ብለዋል። የባለስልጣኑ ሠራተኞችን ጨምሮ የስራ ሃላፊዎች "እንደርሳልን፤ እኔም እጠነቀቃለሁ" በሚል መሪ ቃል ለአሽከርካሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም