ሰላማዊ የትምህር ስራ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ

62

ኢዜአ ህዳር 30/2012 አንድነታቸውን በማጠናከር በተቋሙ ውስጥ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ 14ኛውን የብሄር ብሔረሰቦች በዓል በተቋሙ ግቢ አክብረዋል፡፡

በበዓሉ ስነስርዓት ወቅት ተማሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት በተማሪዎች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት በዩንቨርሲቲው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር አስችሏል፡፡

ከተማሪዎች መካከል ተማሪ መኳንንት ባዬ በሰጠው አስተያየት በዩንቨርሲቲው ውስጥ በተማሪዎች መካከል ያለው አብሮነትና አንድነት የተጠናከረ መሆኑን ገልጿል፡፡

"ይህም የመጣንበትን ዓላማ እንድናሳካ ከማስቻሉም በተጨማሪ ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተምሳሌት እንድንሆን ያስችላል" ብሏል፡፡

በቀጣይም በተማሪዎች መካከል ያለውን ብዝሃነት በማስጠበቅና አንድነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር ለዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በኩሉን እንደሚወጣም ተናግሯል፡፡

ሌላዋ ተማሪ ሐይማኖት ማሩ በበኩሏ "በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል መከበሩ አንዳችን የአንዳችን ባህል እንድናውቅ ያስችለናል" ብላለች፡፡

በዓሉ ሁሉም ብሔር ብሄረሰቦች የራሳቸውን ቋንቋ ፣ ባህላዊ የአለባበስ ሥርዓትና ወጎች በእኩልነት የሚያሳዩበትን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጻለች፡፡

በተለይም በመካከላቸው ያለው የእህትማማችነትና ወንድማማችነት መንፈስ በግቢው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻዋን እንደምትወጣም ተናግራለች፡፡

የመማር ማስተማሩ ስራ ስኬታማነቱ ሁሉም የግቢው ማህብረሰብ መስራት እንደሚጠበቅትም ጠቁማለች፡፡

"በዩኒቨርሲቲው ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ትምህርታችንን ያለ ስጋት እንድንማር አስችሎናል" ያለችው ደግሞ ተማሪ ፀሐይ ዛይድ ነች፡፡

በቀጣይም ይህንን መልካም ግንኙነት በማጠናከር ከቤተሰቦቻቸው የተቀበሉትን አደራ ተግባራዊ በማድረግ የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት በትኩረት እንደሚማሩ ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሰቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በበኩላቸው  እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን ሰላማዊ መማር ማስተማር ቀጣይነት እንዲኖረው ተቋሙ  በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በተለይም ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ሂደት ሰላማዊና ተማሪዎችም የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ከግቢውና  ከአካባቢው ማህበረሰብ  ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች  የመጡ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ ብዝሃነትን ለማስጠበቅና አብሮነትን ለማጠናከር ትኩረት መሰጠታቸውን አስረድተዋል፡፡

ተማሪውም  የመጣበትን የትምህርት ዓላማ ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዓሉ በዩኒቨርሲቲው የተከበረው "ህገ መንግስታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም " በሚል መሪ ሀሳብ ሲሆን በተማሪዎች የተዘጋጁ የተለያዩ  ብሔር ብሔረሰቦች  ባህላዊ ትርኢቶች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም