"ሠላም በዓለም ላይ ከመስፈኑ በፊት ሠላምን በልቦናችን እናኑር" የዓለም የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

72
ኢዜአ ህዳር 30/2012 "ሠላምን በዓለም ላይ ከማስፈን ቀድሞ በልቦናችን ውስጥ ልናሰፍን ይገባል ሲሉ የዓለም የሠላም ኖቤል ተሸላሚ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ምስራቅ አፍሪካ የሃያላን የጦር ሰፈርና የሽብርተኞች መፈንጫ መሆን የለባትም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን በስፍራው ተገኝተው ሲቀበሉ ኢትዮጵያን፣ ኤርትራዊያንን፣ አፍሪካንና ሰላም ወዳድ ህዝቦችን ወክለው በመቀበላቸው ደስታቸውን ገልጸው፤ ለሽልማቱ በቀዳሚነት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አመስግነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገራት የእርስ በርስ ጦርነት በወታደራዊ ኃላፊነት በተሳተፉባቸው ጦር ሜዳዎች ከትዝብታቸው መካከል የወንድማማቾች መገዳደልን፣ የንጹሃንን እልቂት፣ በዜጎች ላይ ያሳደረውን ጸያፍ ገጽታ አንስተዋል። የሁለቱ አገራት ጦርነት ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች መቅጠፉን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አካል ማጉደሉን፣ ሺዎችን ማፈናቀሉን፣ መሰረተ ልማትና ንብረት መውደም፣ መባረርና ሃብት መወረስን ያስከተለውን አስከፊ ገጽታ በአካል መመልከታቸውን አስታውሰዋል። ከጦርነቱ በኋላም አገራቱ ለሁለት አስርት ዓመታት 'በሠላም አልባ ጦርነት' ግንኙነት መቆየታቸው ለሁለቱ አገራት ዜጎች ዕለታዊ ፍርሀትና ሰቆቃ ማትረፉን፣ ለአካባቢው አገራት ሠላምና ጸጥታም አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስታውሰዋል። በአጠቃላይ የጦርነት መራርነትና የሠላምን ጣዕም በስፍራው መታዘባቸውን በመግለጽ፤ ለመንበረ ስልጣን ሲበቁ የሁለቱን አገራት ሠላም መፍታት ቀዳሚ ተልዕኮ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም ሁለቱ አገራት ህዝቦች ከጋራ ጠላታቸው ድህነት በስተቀር ህዝቦች ጠላት እንዳልነበሩ፤ ከጦርነት ይልቅ አብሮ መበልጽግን የሚሹ መሆናቸውን በማመን፤ አሁን ላይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ተመልሶ በቴሌኮሚነኬሽንና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ፕሮጀክቶች ተሳስረው ወደቀደመ ሠላምና አብሮነት መመለሳቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል አገር መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋና የመናገርና የመጻፍ ነጻነት እንዲኖር የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል። ሠላም ከልብ የሚመነጭ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም ለማምጣት ችግኝ ተክሎ እንደማሳደግ ጊዜና ጥረት የሚሻ ጉዳይ እንጂ እንደ ጦርነት በደቂቃዎች የሚሆን እንዳልሆነ አብራርተዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሙሉ ቅንነትና ሰብዓዊነት በሁሉም ልብ ውስጥ በመኖሩ በሙሉ ተስፋና እምነት ሁሉም መተግበር እንደሚገባው ገልጸዋል። ወደፊትም ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ሙሉ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፤ ለዚህም ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተሳስረው የሚበለጽጉበት፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገር በቀል እሴቶች ላይ የተመሰረተ መደመር የተሰኘ አገር በቀል ፍልስፍናቸውን አንስተዋል። ፍቅር፣ ይቅርታና እርቅ የሠላም አዕምዶች መሆናቸውን ገልጸው፤ እምነት፣ ሰብዓዊነት፣ መረዳዳት፣ ትዕግስት፣ ምስጋናና መተባባር ከአንድ ምንጭ የሚቀዱ እሴቶች እንደሆኑና፤ እነዚህ እሴቶች ካደጉበት ቤተሰብና አካባቢ የወረሱት መሆኑን ተናግረዋል። ምድረ ቀደምቷ፤ ባለ 13 ወር ጸጋዋ ኢትዮጵያ ለአራት ሺህ ዓመታት በነጻነት የኖረችው ኢትዮጵያዊያን በእምነትና በአንድነት በመኖራቸው መሆኑን ገልጸው፤ መደመርም በሰላምና እርቅ ላይ የተመሰረተ፣ በብዝሃነት ሁሉን አካታች ፍልስፍና ነው ብለዋል። በመደመር ፍልስፍና ከኢትዮጵያዊያን አልፎ ከጎረቤት አገራት ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ትኩረቱ መደረጉን አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ የሃያላን መንግስታት የጦር ሰፈር ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን፤ አካባቢው የሽብርተኞችና ጽንፈኞች ኮቴም የማይለቀው መሆኑን ገልጸው፤ ቀንዱ የሰላም አካባቢ የሃያላኑና የጽንፈኞች ሽኩቻ ማዕከል መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል። ሠላም የሕይወት አካል እንደሆነ እምነታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሠላም ሰባኪያኑ ዜጎች በሠላም ውስጥ እንዲኖሩ፣ ከቤተሰብ እስከ አገራት የሠላም ባህል እንዲዳብር፤ በመካከላቸው ሠላም እንዲያሰፍኑና በሠላም ውስጥ እንዲኖሩ ጥሪ አቅርበዋል። በሌላ በኩል ሰላምን ለማስፈን በተለይም 70 በመቶው ወጣት በሞላበት አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ፍትህንና መልካም አስተዳደርን ማስፈን፤ ሙስናን መከላከል፣ እንደሚያሻ አሳስበዋል። በመሆኑም ለሁሉም ዜጎች ፍትህ፣ መብትና ዕድሎች በእኩልነት እንዲኖር ዓለም ሁሉ በጋራ እንዲተባበር ጠይቀዋል። የዘረኝነትና የመከፋፈል ሰባኪዎችንም በጋራ በመመከት የጋራ መግባባት፣ አብሮነት፣ መቻቻል በመደመር መተግበር ይገባልም ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም