ብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሄራዊነትን በማጉላት ጠንካራ አገረ መንግስት ለመገንባት እንደሚያስችል ምሁራን ገለጹ

77

ኢዜአ ህዳር 30/2012 ብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሄራዊነትን በማጉላት ጠንካራ አገረ-መንግስት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) አባል ድርጅቶች ከሆኑት ውስጥ ሶስቱ እና አጋር የነበሩ አምስት ድርጅቶች በመዋሃድ 'ብልጽግና' የተሰኘ ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ-ም መፈጸማቸው ይታወቃል።

የድርጅቶቹ ወደ ውህደት መምጣትና አገራዊ ፓርቲ መመስረት ህብረ ብሔራዊ ጠንካራ አገረ መንግስት ለመመስረት ሚናው የጎላ እንደሚሆን ምሁራን ገልጸዋል።

በአመራር ጥበብ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አሰፋ በየነ እንደሚሉት፤ ኢህአዴግ ለረጅም ዓመታት ውህድ ፓርቲ ለመመስረት እንደሚፈልግ ሲገልጽ ቢቆይም ተግባራዊ ሳያደርግ በመቆየቱ በየጊዜው የመልካም አስተዳደርና የአሳታፊነት ጥያቄዎች ሲነሱበት ነበር።

ሁሉም ዜጎች በአገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቅድሚያ የድርጅቱን ችግር መፍታት ተገቢ እንደሆነም ገልጸዋል።

''በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ አዲስ ነገር በማስቀመጥ ለውጥ አይመጣም'' ሲሉ ተናግረዋል።

አገራዊ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ ስልቶችን መተግበርና አማራጮችን መከተል እንደሚያስፈልግ ዶክተር አሰፋ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ያላቸውን ልዩነት ጠብቆ በጋራ ጉዳያቸው ላይ ጠንካራ አንድነት እንዲኖራቸው ለማስቻል የተሰራው ስራ አነስተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

አሜሪካ ከተለያዩ አገሮች ዜጎችን በማምጣት የዜጎችን ዕውቀት ለልማት በመጠቀም ብዝሃነት ያለውን ጥንካሬ በተግባር እያሳየች መሆኑንም ለአብነት አንሰተዋል ዶክተር አሰፋ።

በኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰብ ቢኖርም ያለውን ዕውቀትና ጥበብ ተጠቅሞ በጋራ መስራትና ማደግ ያልተቻው ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ትኩረት አድረጎ በመሰራቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

አዲሱ  ውህድ ፓርቲ  ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክር አገረ መንግስት መገንባት እንደሚያስችል ዶክተር አሰፋ አንስተዋል።

የፌዴራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሃይለየሱስ ታዬ ብልጽግና ፓርቲ ለአገራዊ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ ለአገራዊ አንድነትና ጥንካሬ የጎላ ሚና የሚጫወት መሆኑን ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮን በመግለጽ ያስረዳሉ።

ክልላዊ ፓርቲዎች በበዙ ቁጥር ዋናውን አገራዊ ጉዳይ ወደ ክልል የመጎተት ዕድሉ እንደሚሰፋ የገለጹት ዶክተር ሃይለየሱስ፤ የፌዴራል ስርዓትን የሚከተሉ አገሮች ውስጥ አገራዊ ፓርቲዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ብዝሃነት ባለበት አገር ውስጥ በስምምነት ላይ አገራዊ ፓርቲ መመስረት የተለመደ መሆኑን ገልጸው፤ ''ውህድ ፓርቲው የፌዴራል ስርዓቱን የበለጠ የተማለከለ ያደርገዋል'' ብለዋል።

  ውህድ ፓርቲው የፌዴራልና የክልል መንግስታት እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር እንደሚሆንም ነው ምሁራኑ ያነሱት።

በአገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ፓርቲ መመስረት አሃዳዊ ስርዓትን ያመጣል የሚሉ ሀሳቦች ፓርቲና መንግስትን ለይቶ የማየት ችግር መሆኑን ገልጸዋል።

ከህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ 'ህወሃት' ውጪ ሁሉም የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ብልጽግና ፓርቲን ለመመስረት ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም