ብክለት ለመቀነስ የተቀመጡ ደረጃዎች አተገባበር አስመልክቶ የተካሄደ የቁጥጥር ግኝት ይፋ ተደረገ

61
ኢዜአ ህዳር 30 /2012 የፋብሪካዎች የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ የተቀመጡ ደረጃዎችና መለኪያዎች አተገባበርን አስመልክቶ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ያካሄደው የቁጥጥር ግኝት ይፋ አደረገ። ተቋሙ ግኝቱን ይፋ ያደረገው  ዛሬ በአዳማ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ነው። በዚህ ወቅት በተቋሙ የሴቶችና ህጻናት አስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰብለወርቅ ታሪኩ እንዳስታወቁት አስፈጻሚ  አካላት የአካባቢ ብክለትን አስመልክቶ እየሰሩ ያሉትን ተከታትሎ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ የእርምት እርምጃ መውሰድ በማስፈለጉ ቁጥጥር ተካሂዷል፡፡ ቁጥጥሩ የተከናወነባቸውም አዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች ፣ ትግራይ፣አማራ፣ ኦሮሚያ ፣ደቡብና  ሐረሪ ክልሎች  በተመረጡ የመንግስት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች  ነው። በእነዚህ አከባቢዎች በተያዘው ዓመት በተደረገው ቁጥጥር በየደረጃው ያሉ ተቋማት፣ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ከመግባታቸው በፊት የአከባቢ ተጽዕኖ፣ በህጻናትና ነፍሰጡር እናቶች ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመገምገም የሚያስችል አሰራር እንደሌለ በክፍተት መመልከት እንደተቻለ ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል። በተለይ የአካባቢ ብክለት ለመከለከልና ለመቆጣጠር በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ አደረጃጀትና በቂ የሰው ሃይል ባለመኖሩ ለክትትልና ድጋፍ ስራ ክፍተት መፍጠሩን አመልክተዋል። በክልሎች የወጡ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥርና የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጆች ወደ ተግባር እንዲገቡና የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ደንብና መመሪያ ሊወጣላቸው እንደሚገባ ግኝቱ የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱ  የብክለት ደረጃው አሳሳቢ  ደረጃ ባይደርስም በከተሞችና ፋብሪካዎች በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች የድምጽ፣የአየርና የፍሳሽ ብክለቶች ተስተውሏል። በፍሳሽ ብክለት ረገድ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ከሌላቸው የመኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ፣ ከቆዳና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችና ከሆቴሎች የሚወጣ ለጤና አስጊ  መሆናቸው ተጠቁሟል። ከጤና ተቋማት፤ከቢራና ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካዎችና ከቡና መፈልፈያ ድርጅቶች የሚለቀቁ ፍሳሾችም እንዲሁ። ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘም በሲሚንቶ ፋብሪካና የድንጋይ ጠጠር በሚያመርቱ ፋብሪካዎች አለቶችን ለመናድ የሚጠቀሙበት ደማሚት የሚፈጥረው የብናኝ ብክለት ዋንኛው ነው። ከቄራዎች፣ ከቆዳና በጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች አካባቢ የሚታይ መጥፎ ሽታ ፣  ከተሸከርካሪዎችና ፋብሪካዎች የሚለቀቁ ጭሶች የአየር ብክለት መንስዔ ቦታዎች ተብለው የተለዩ ናቸው። ዳይሬክተሯ እንዳመለከረቱት ችግሩን ለመከላከል በክልሎቹ ኃላፊነት የተሰጠው አካል ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ተፈፃሚ የሚሆኑባቸው ዝርዝር ደንቦችና መመሪያዎች እንዲወጡ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ በተለይ አዳዲስ የሚቋቋሙ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት እንዲያደርጉ እየተደረገ ያለው ጥረት በጠንካራ ጎን አንስተው በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። በአካባቢ ላይ ብክለትን ያስከተሉ ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ጅምር መኖሩ፣ አንዳንዶቹም ብክለት የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ያላቸው ፈቃደኝነት ግኝቱ ያመላከት ሌላው ጠንካራ ጎን ነው። የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በበኩላቸው ተቋሙ ባለፉት ዓመታት ህገመንግስቱ ለዜጎች ያጎናጸፋቸው ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን በመከታተልና በመቆጣጠር ለክፍተቶች የመፍትሄ ሃሳቦችን በመጠቆም አፈጻጸማቸውን ሲከታተል መቆየቱን አስታውሰዋል። የምክክር  መድረክም በቁጥጥር ወቅት የተለዩ የህግና የአሰራር ክፍተቶች እንዲታረሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግብባት ላይ ለመድረስ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል። የምክክር መድረኩ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ ሲሆን አሁን ላይ  በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ከመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተካሄደ የቁጥጥር ግኝት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም