በአፋር የትራኮማ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

75
ኢዜአ ህዳር 30 ቀን 2012 በአፋር ክልል በ19 ወረዳዎችና ሦስት ከተማ አስተዳደሮች የትራኮማ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ። በክትባቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተመልክቷል። በክልሉ ጤና ቢሮ የተላላፊ በሽታዎች መከላከል ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ሞሚና አብደላ እንዳሉት ትራኮማ (የዓይን ማዝ) "ችላሚዲያ-ትራኮማቲስ" በተባለ የበሽታ አምጭ ባክቴሪያ የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ነው። ባክቴሪያው ከሰው ወደሰው የሚተላለፈው በቀላል ንክኪ፣ በዝንቦች እንዲሁም ከዓይን-ናር ጋር ንክኪ ያላቸውን እቃዎች በጋራ በመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል። በሽታው በቂ የንጹህ ውሃ አቅርቦት በሌለባቸው እንደአፋር ክልል ባሉ አካባቢዎች በስፋት እንደሚስተዋል መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ወይዘሮ ሞሚና ተናግረዋል። ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በ19 የክልሉ ወረዳዎች በተደረገ ጥናት ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ለበሽታው ተጋላጭ መሆናቸው ታውቋል። "ይህም ትራኮማ በአፋር ዋነኛ የህብረተሰብ ጤና ጠንቅ ከሆኑት ውስጥ አንዱ እንደሆነ ያሳያል" ብለዋል። በሽታውን ለመከላከል ከ19 ወረዳዎች በተጨማሪ የአይሳኢታ፣ ዱብቲ እና አበአላ ከተማ አስተዳደሮችን ያካተተ ክትባት ከዛሬ ጀምሮ መስጠት መጀመሩንና አስከ ታህሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል አመልክተዋል። ክትባቱ በጤና ተቋማትና ቤት ለቤት በመሄድ እንደሚሰጥ ገልጸው በእዚህም ከ1 ሚሊዮን 17 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል። የመካለከያ መድሃኒቱ እንደየእድሜ ክልሉ በተያያዝ ምክንያቶችን ታሳቢ በማድረግ በአይን ጠብታ፤ በሽሮብና በአንክብል መልክ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል ወይዘሮ ሞሚና እንዳሉት ለነፍሰ ጡር እናቶችና ከ6 ወር በታች ለሆናቸው ህጻናት መድኃኒቱ በዓይን ጠብታ መልክ የሚሰጥ ሲሆን ከ6 ወር በላይ እስከ 7 ዓመት ለሆናቸው ልጆችም መድኃኒቱ በሽሮፕ መልክ  እንደሚሰጥ አብራርተዋል። ከዚህ የእድሜ ክልል ውጭ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መከላከያ መድኃኒቱ በእንክብል መልክ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በ2020 ትራኮማን ከዓለም ለማጥፋት አቅዶ እየሰራ ያለው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ትራኮማ በኢትዮጵያ ዜጎችን ለዓይነ-ስውርነት በማጋለጥ በ2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በሽታውን አስመልክቶ በየጊዜው የሚወጡ ዓለም አቅፍ ጥናቶችም ትራኮማ በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናትን እንደሚያጠቃ ያሳሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም