በዞኑ አርሶ አደሮች የደረሰ ሰብላቸውን ፈጥነው በመሰብሰብ ወደ መስኖ ልማት ገብተዋል

112
ኢዜአ ህዳር 30/2012 በመኸሩ ወቅት ያለሙትን ሰብል ፈጥነው በመሰብሰብ ፊታቸውን ወደ መስኖ ልማት ማዞራቸውን በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ገለጹ። በዞኑ ከህዳር ወር 2012ዓ.ም መግቢያ ጀምሮ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮቹ ሦስት ሺህ 471 ሄክታር ማሳ በመስኖ እየለሙ እንደሚገኙ ተመልክቷል። ከግንባር ቀደም አርሶ አደሮቹ መካከል በመደባይ ዛና ወረዳ የባህራ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አቶ በረከት አረጋዊ እንዳሉት፣ዘንድሮም የደረሰ ሰብላቸውን ፈጥነው በማንሳት በግማሽ ሄክታር ማሳ ቀይ ሽንኩርት በመስኖ ማልማት ጀምረዋል። የመስኖ ልማት ልምድ በማዳበራቸው ማሳቸው በዓመት ሦስት ጊዜ በማልማት የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል። በየዓመቱ ባገኙት ገቢም በሰለክላካ ከተማ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት መገንታቸውን ጠቅሰዋል። የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር በላይ መብራህቶም በበኩላቸው፣በመኸር ወቅት በጤፍ የሸፈኑትን አንድ ሄክታር ማሳቸው ፈጥነው በማንሳት ፊታቸውን ወደ መስኖ ማዞራቸውን ተናግረዋል። በዚህም ገበያ ተኮ የሆነው ቀይ ሽንኩርት ማልማት እንደጀመሩ ገልጸዋል። ከሁለት ዓመት በፊት በሩብ ሄክታር ማሳ የጀመሩትን የመስኖ ልማት ዘንድሮ ወደ አንድ ሄክታር በማስፋት እንደቀጠሉም አመልክተዋል። በታህታይ ቆራሮ ወረዳ የሰመማ ቀበሌ ሴት አርሶ አደር ህልፍቲ አባይ በሰጡት አስተያየት የውሃ አማራጮችን ለመስኖ ልማት ተጠቅመው የአንድ ሄክታር ማሳቸውን በኩታ ገጠም እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዞኑ በበጋው ወቅት የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃን በመጠቀም ዘጠኝ ሺህ ሄክታር ማሳ በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዞኑ አስተዳደር የኩታ ገጠም መስኖ ልማት አስተባባሪ አቶ አስተባባሪ አቶ ሚኪኤለ ተስፋይ ናቸው። ከዚህም እስካሁን ከሦስት ሺህ 400 ሄክታር በላይ በመስኖ እየለማ መሆኑን አስረድተዋል። እየለማ ከሚገኘውም ከአንድ ሺህ 500 ሄክታር በላይ በኩታ ገጠም አሰራር እየለማ የሚገኝ ነው። በተጀመረው የመስኖ ልማት ከ6 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ባለፈው ዓመት የበጋ ወቅት በሁለት ዙር በመስኖ ከለማው መሬት ከአራት ሚሊዮን 700ሺህ  ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም