በጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የጤና ኬላ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው

146
አዲስ አበባ ሰኔ15/ 2010 በጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችል የጤና ኬላ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ በአለም የጤና ድርጅት እውቅና ተችሮት የበርካታ የአፍሪካ አገሮችን ቀልብ በመሳብ ልምድ ለመቅሰም ባለሙያዎችን እየላኩ የሚመለከቱት የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር በአገሪቱ ለተመዘገበው የጤና ዘርፍ ውጤት ድርሻው ከፍተኛ ነው። መርሃ ግብሩ ውጤታማ ቢሆንም የጤና ኬላዎች መፈራረስ፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላትና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሌሎች ስራዎች መጠመድ ሳቢያ መደበኛ ስራው እንዲዳከም ማድረጉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያረጋግጣል። በሚኒስቴሩ የጤና ኤክስቴንሽንና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ እስራኤል አታሮ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መርሃ ግብሩ አገሪቱ የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች ቀድማ እንድታሳካና የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ አስችሏል። ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የጤና ኬላዎች መፈራረስና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አነስተኛ መሆኑን ጨምሮ መርሃ ግብሩ ያሉበት ችግሮች ተለይተው መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የጤና ኬላዎች መፈራረስ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዳይሰጥ ማድረጉን የተናገሩት አቶ እስራኤል ጤና ኬላዎችን በመገንባት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ካለው የህብረተሰቡ የኢኮኖሚ ደረጃና የአኗኗር ዘይቤ ጋር እንዲመጥን አድርጎ ለመቃኘት ፍኖተ ካርታው እንደሚረዳ ተናግረዋል። የፍኖተ ካርታው ዝግጅት በተያዘው በጀት አመት እንደሚጠናቀቅ ያብራሩት አቶ እስራኤል በቀጣዩ በጀት አመት በፍኖተ ካርታው መሰረት ወደተግባር እንደሚገባ ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ጤና ኬላዎች ውስጥ የሚታደሱና እንደአዲስ ፈርሰው የሚገነቡ እንደሚኖሩም ነው የተናገሩት። በፍኖተ ካርታው መሰረት የሚሰሩት የጤና ኬላዎች የክፍሎች ብዛት ከነባሮቹ የበለጠ እንደሚሆንና አንዱ ጤና ኬላ ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀው ለወደፊት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጭምር እንደሚይዝ ተናግረዋል። መርሃ ግብሩን ለማጠናከር ለባለሙያዎች የትምህርት እድል በመስጠት የተሻለ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት። በጤና ኬላዎቹ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በጥራትና ብዛት ለማሻሻል ሁሉም ክልል ከአዲሱ በጀት አመት ጀምሮ የግብዓት አቅርቦት ማሻሻያን በእቅድ ውስጥ አካቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል። የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩን ይበልጥ ለማጠናከር በልማት ቡድን ለተደራጁ ሶስት ሚሊዮን እናቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል። የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር በገጠር በ1997 ዓ.ም፣ በከተማ ደግሞ በ2002 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎች በዘርፉ እየሰሩ ይገኛሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም