በትግራይ ደቡባዊ ዞን አምስት ወረዳዎች የተከሰተውን ተምች ለመከላከል እየተሰራ ነው

56
ማይጨው ሰኔ 15/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን አምስት ወረዳዎች የተከሰተውን መጤ የአሜሪካ ተምች ለመከላከል እየተሰራ ነው። በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሃይለ ካሳ ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት ተምቹ በዞኑ በሚገኙ 28 የገጠር ቀበሌዎች ተከስቷል። ተምቹ ቀደም ሲል በዞኑ የመስኖ ልማት በሚካሄደባቸው አካባቢዎች ተከስቶ በወቅቱ የመከላከል ስራ በመከናወኑ መቆጣጠር ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና በዞኑ ባለፈው ሚያዝያ ወር በጣለው ዝናብ በአከባቢው የበቀለው ሳር ለተምቹ መፈልፈል ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ዳግም እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል። “በአሁኑ ጊዜ የተምቹን መስፋፋት ለመግታት በተወሰኑ አካባቢዎች ህብረተሰቡ በእጅ እየለቀመ ጉድጓድ ውስጥ በመቅበርና በመግደል ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው'' ብለዋል፡፡ በዞኑ በተወሰኑ ወረዳዎች ደግሞ ኬሚካል በመርጨት ተምቹን ሳይዛመት ባለበት የመግደል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜም በየወረዳው ተምቹን ለመከላከል የሚያስችል በቂ መድሃኒትና የመርጫ መሳሪያዎች አቅርቦት በመኖሩ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለመቆጣጠር እንደሚቻል ነው ያስታወቁት፡፡ በዞኑ ተምች ሊከስት እንደሚችል በመገመቱ ለአካባቢው አርሶአደሮችና ባለሙያዎች አስቀድሞ ስልጠና በመስጠት የመከላከሉን ስራ በመጀመሩ እስካሁን የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ገልጸዋል። “በራያ አዘቦ ወረዳ በሚገኙ አምስት የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የአሜሪካ መጤ ተምች የተከሰተ ቢሆንም ስርጭቱ እምብዛም በመሆኑ በገበሬው ጉልበት የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው'' ያሉት ደግሞ የወረዳው ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የአዝርዕት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ማናዬ ጌታሁን ናቸው። በኦፍላ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የአዝርዕት ጥበቃ ባለሙያ አቶ አያሌው ሽፈራው በበኩላቸው፣ የአሜሪካ ተምቹ የተከሰተው በወረዳው በሚገኙ ሓሸንጌ፣ ህጉምብርዳ፣ መንከረና አዲጎሎ በተባሉ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው ብለዋል። ተምቹን ለመከላከል የሚያስችል የኬሜካል መድሃኒት ወደ ገጠር ቀበሌዎቹ በማዳረስ የመከላከሉ ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን ነው አቶ ሽፈራው ያስረዱት፡፡ “ተምቹ በአከባቢያቸው የተከሰተ ቢሆንም የመኽሩ ሰብል ገና ያልጀመረ በመሆኑ የደረሰ ጉዳት የለም'' ያሉት ደግሞ በራያ አዘቦ ወረዳ የሓዳ አልጋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አድሃና ሓዲስ ናቸው፡፡ ይሁንና ተምቹን በፍጥነት በመራባት የአገዳ ሰብሎችን የሚያጠቃ መሆኑን በወሰዱት ስልጠና በመረዳታቸው ተምቹን በእጅ በመልቀም የማስወገድ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። “የኬሚካል መድሃኒትና የመርጫ መሳሪያ እየቀረበልን በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተምቹን ለማጥፋት ተባብረን እየሰራን ነው'' ብለዋል አርሶ አደሩ፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም