የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መድሃኒቶችን በቅመማ በማሻሻል ፈዋሽነታቸውን ማሳደግ መቻሉን አስታወቀ

46
ኢዜአ ህዳር 30 / 2012 ዓ.ም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በህክምና ተቋማት የሚታዘዙ መድሃኒቶችን በቅመማ በማሻሻል ፈዋሽነታቸውን በማሳደግና ጉዳታቸውን በመቀነስ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን አስታወቀ። ሆስፒታሉ በመድሃኒት ቅመማ ዘርፍ ለእጅና ለቁስል ማጽጃነት በሚያገለግለው አልክሆልና ለቆዳ በሽታ የሚታዘዙ መድሃኒቶችን አሻሽሎ በመቀመም ውጤታማ ተግባር ማከናወኑን ገልጿል። የሆስፒታሉ ዋና ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ለኢዜአ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በምርምር ስራዎች እየተሳተፈ ይገኛል። በዚህም ለበርካታ ዓመታት ለህክምና አገልግሎት ሲውል የቆየው አልክሆል የአሲድ መጠኑ 96 በመቶ በመሆኑ በቆዳና በእጅ ላይ የጎንዮሽ የጤና ጉዳት የሚያስከትል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም ሆስፒታሉ ባቋቋመው የመድሃኒት መቀመሚያ ማእከል ባለፉት ዓመታት ባደረገው ምርምር ምንም አይነት የእጅና የቆዳ ጉዳት የማያስከትል አልክሆል በመቀመም ስራ ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡ ''በቅመማ የተገኘው አዲሱ አልክሆል ከዚህ ቀደም የእጅ ድርቀትና መሰንጠቅ የጤና ችግር ሲያስከትል የቆየውን ነባሩን አልክሆል ለመተካት የሚስችል ነው'' ብለዋል፡፡ አልክሆል በህክምናው ዘርፍ የቆዳ ላይ ቁስሎችን በቅድሚያ ከጀርሞች ነጻ በማድረግ ህክምና ለመስጠት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርና ጎጂ ተዋሲያንም ለማስወገድ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። ሆስፒታሉ በሌላም በኩል የጉሉኮስን የመጠንና የጥራት ደረጃ የሚያሻሽል ምርምር በማካሄድ ለህጻናት አዲስ የጉሉኮስ ምርት አዘጋጅቶ ለህክምና ስራ እንዲውል ማድረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት ለተለያዩ የቆዳ በሽታዎች በቅባት መልክ የሚታዘዙ መድሃኒቶችን በቅመማ በማሻሻል በፈዋሽነታቸውና በጥራታቸው የተሻሉ መድሃኒቶችን በመቀመም ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቆዳ ላይ ለሚከሰቱ ለእከክ፣ ለብጉር፣ ለጭርትና ማዲያት ለመሳሰሉት በሽታዎች በስፋት ሲውሉ የቆዩ መድሃኒቶችንም በቅመማ በማሻሻል ለህክምና አገልግሎት እንዲውሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በገጠማቸው የመቁሰል አደጋ በሆስፒታሉ የቁስል ህክምና በማድረግ ላይ የሚገኙት አቶ አለባቸው መኮንን ለቁስል ማጠቢያነት ጥቅም ላይ የዋለው አልክሆል በጣም የሚያቃጥልና የሚለበልብ ቆዳም የሚያደርቅ ነበር ብለዋል፡፡ አሁን ላይ በሆስፒታሉ የቀረበው አዲሱ አልክሆል ቆዳ እንዲደርቅና እንዲሰነጠቅ አያደርግም፤ ጎጂ ተዋስያንን በማጽዳት በኩልም የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ያሉት ደግሞ ሌላው ታካሚ አቶ ይበይን ታዲዎስ ናቸው፡፡ ሆስፒታሉ የታማሚዎችን ስቃይና የመድሃኒት ግዢ ወጪዎችን ጨምሮ የመድሃኒቶችን ፈዋሽነትና የጎንዮሽ ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ምርምሮችን በስፋት እያካሄደ እንደሚገኝም ዳሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም