በንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ ሆነናል---በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች

56
ኢዜአ ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም በአካባቢያቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአቤ ደንጎሮ እና የጅማ ገነቲ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ። በዞኑ አቤ ደንጎሮ ወረዳ ጨሩ ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ ሙሉነሽ ነጋሽ እንዳሉት ኪዚህ ቀደም በጎለበተ ምንጭ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ቢሆኑም ውሃው ከርቀት ስለሚመጣ በልማት ሥራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲደርስ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው ተገንብቶ ለአገልግሎት በበቃው የውሃ ተቋም ውሃ በአቅራቢያቸው በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል። ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ ከማል አህመድ በሰጡት አስተያየት "የውሃ ተቋሙ አገልግሎት መስጠት መጀመር ከዚህ ቀደም ሕፃናት በኮሌራ እና በተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች ይታመሙ የነበረውን ሁኔታ ያስቀራል" ብለዋል። ለከብቶች መጠጥና ለልብስ የሚጠቀሙበት ውሃ አንድ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ከማል በአሁኑ ወቅት ችግራቸው በመቀረፉ መደሰታቸውን ገልጸዋል። በዞኑ የጅማ ገነቲ ወረዳ ሁንዴ ጉድና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጎንፈ ገርባባ በበኩላቸው እንዳሉት ቀደም ስል ወራጅ ውሃ ሲጠቀሙ ለታይፎይድና ለሆድ ሕመም በሽታዎች ይጋለጡ ነበር። በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የውሃ ተቋም ጤንነታቸው ከመጠበቅ ባለፈ ውሃ ለመቅዳት ያባክኑት የነበረውን ጊዜና ጉልበት ማስቀረቱን ተናግረዋል። የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውሃና ኢነርጂ ጽዕፈት ቤት የእቅድና በጀት ባለሙያ አቶ ባቡ ሰንጥ እንደተናገሩት ግንባታቸው በ2009 እና በ2011 ዓ.ም የተጀመሩ ሦስት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። የውሃ ፕሮጀክቶቹ በአቤ ዶንጎሮ እና በጅማ ገነቲ ወረዳዎች ከ4 ሺህ 540 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አመለክትዋል። የውሃ ተቋማቱ በግፊት፣ በሶላርና በሞተር ኃይል የሚሰሩ ሲሆኑ ለፕሮጀክቶቹ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ወጪ መደረጉንም አመልክተዋል። እንደአቶ ባቡ ገለጻ በተያዘው በጀት ዓመት ከዞንና ከክልል በተመደበ በጀት 30 የውሃ ፕሮጀክቶች፣ በሕዝብ ተሳትፎ እና በወረዳ በጀት 127 ፕሮጀክቶች ለመገንባት ታቅዶ ወደተግባራዊ ሥራ ተገብቷል። ከሚገነቡት የውሃ ፕሮጀክቶቹ መካከል በግፊት ኃይል የሚሳብ ውሃ፣ ጥልቅ ጉድጓድ፣ መካከለኛ እና አጭር ጉድጓድና ምንጭ ማጎልበት ይገኙበታል። የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት ከ35 እስከ 90 በመቶ መድረሱን አስታውሰው፣ በበጀት ዓመቱ ህብረተሰቡን የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ከ88 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን አመልክተዋል። እነዚህ የውሃ ፕሮጀክቶቹ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደአገልግሎት ሲገቡ ቁጥራቸው 79 ሺህ 552 የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ይሆናሉ። እንደባለሙያው ገለጻ የዞኑ የመጠጥ ውሃ ሽፋን አሁን ካለበት 72 በመቶ ወደ 81 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም