የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን አሠራር የሚፈትሽ የጥናት ኮሚቴ ተቋቋመ

72
አዲስ አበባ ሰኔ15/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን አደረጃጀት እና የአሠራር ችግር የሚፈትሽ የጥናት ኮሚቴ ተቋቋመ። ኮሚቴው የተቋቋመው አዲስ የተመረጠው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ ላይ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ለኢዜአ አስታውቋል። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን አደረጃጀት እና የአሠራር ችግር የሚፈትሽና የመፍትሔ ሀሳቦችን የሚጠቁም ሰነድ ላይ ውይይት  አካሂዷል። ለውይይት የቀረበውን ሰነድ መሰረት በማድረግ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ስር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ እንዲተገበር የሚረዳ ጥናት ማካሄድ እንደሚገባና ለጥናቱም አንድ ኮሚቴ እንዲቋቋም ከመግባባት ላይ መደረሱ ተጠቅሷል። በዚህም መሰረት ጥናቱ እንዲካሄድ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉንና ኮሚቴውም ጥናቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ የሚገባበት መንገድ እንዲመቻች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መወሰኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን አደረጃጀት እና የአሠራር ችግር የሚፈትሽ የጥናት ኮሚቴ የመቋቋም ውሳኔ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ አመራር ወደ ስራ ከገባ በኋላ የወሰነው ነው። የአገሪቷን የእግር ኳስ ችግር ለማስተካከል ስፖርቱ በዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ሊመራ እንደሚገባው የስፖርቱ ቤተሰብ በተደጋጋሚ የሚያነሳው ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም