ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ መመሪያ ለማዘጋጀት ተስማሙ

79
ኢዜአ፤ ህዳር 30/2012 ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ለህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ መመሪያ ለማዘጋጀት መስማማታቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዋሽንግተን ያደረጉትን ውይይት ትናንት አጠናቅቀዋል። በስብሰባው የተሳተፉት የኢትዮጵያ፣ የግብፅ ና የሰዳን የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም በታዛቢነት የተቀመጡት የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ተወካዮች የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በውይይቶቻቸው ወቅት የአሜሪካን እና የዓለም ባንክን መገኘት ደግፈዋል። በአዲስ አበባ እና በካይሮ ባደረጓቸው ቴክኒካዊ ውይይቶች የተሻለ ውጤት መገኘቱንም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ትናንት በዋሽንግተን ካደረጉት ግምገማ በኋላ በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ባወጡት የጋራ መግለጫ በቀጣይ በአዲስ አበባ እና በካርቱም የቴክኒክ ውይይቶች መመሪያና መተዳደሪያ ደንብ እንዲዘጋጅ መስማማታቸውን ገልጸዋል። የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ደንብ እንዲዘጋጅ ተስማምተዋል። ደንብ እና መመሪያዎቹ በወንዙ ዓመታዊ ተፈጥሯዊ ፍሰት እና ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚለቀቅ የውሃ መጠንን መሰረት ድርቅን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲያካትቱም ስምምነት ላይ ተደርሷል። ድርቅን በተመለከተ የመተዳደሪያ ደንብ እና መመሪያ መዘጋጀቱ ለሦስቱም ሀገራት እንደሚጠቅም ሚኒስትሮቹ መቀበላቸውን ያወጡት የጋራ መግለጫ ያሳያል። ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚዘጋጁትን መተዳደሪያ ደንቦችና መመሪያዎች ኢትዮጵያ ተግባራዊ እንደምታደርግና ዓመታዊ የውሃ ጉዳዮችን በማጤን ሦስቱ ሀገራት ማሻሻያዎችን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተነግሯል። ሦስቱ ሀገራት በአዲስ አበባ እና በካርቱም የሚያደርጓቸውን ቴክኒካዊ ውይይቶች ካጠናቀቁ በኋላ ስምምነታቸውን ለማጠቃለል በፈረንጆቹ ጥር 13 ቀን 2020 ተመልሰው ዋሽንግተን እንደሚሄዱ ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም