እጅ ኳስ ፌዴሬሽኑ በአዲስ አበባ በሚካሄዱ የ15ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የቀን ለውጥ አድርጓል

57
አዲስ አበባ ሰኔ15/2010 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን በአዲስ አበባ በሚካሄዱ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የቀን ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ። በሊጉ የዚህ ሳምንት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ነገ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ፖሊስ ከነገ በስቲያ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ማረሚያ በተመሳሳይ ከቀኑ ሶስት ሰሀት ላይ ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው። ነገር ግን በአዲስ አበባ በሚካሄዱት ጨዋታዎች ላይ የመርሃ ግብር ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ፖሊስ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ማረሚያ ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ መወሰኑን ፌዴሬሽኑ ገልጿል። በክልል ከተሞች የሚካሄዱ ጨዋታዎች ግን በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት የሚካሄዱ ይሆናል። በዚሁ መሰረት ነገ ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ አምስት ሰዓት ከነገ በስቲያ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከመቀሌ ከተማ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብርን ለማስተካከል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የዚህን ሳምንት ጨምሮ የአራት ሳምንታት መርሃ ግብር ቀርተውታል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ22 ነጥብ ሲመራ፣ ፌዴራል ፖሊስ በ18 ነጥብ ሁለተኛ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና መቀሌ ከተማ በተመሳሳይ 17 ነጥብ በግብ ክፍያ ተባላልጠው በቅደም ተከተል ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል። ቡታጅራ ከተማ ሁለት ነጥብ ብቻ ይዞ የመጨረሻው ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም