ጾታዊ ጥቃትን ከሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ጣቢያዎች ማስቆም ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተመክሯል

57
ኢዜአ ህዳር 29/2012 ሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ስፋት በመረዳት ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ጣቢያዎች በሚገኙ ሴቶችና ህጻናት ላይ ስለሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት ስፋት፣ መንስኤዎች፣ መከላከል፣ የህግ ማዕቀፎችና ድጋፎች ዙሪያ ተወያይተዋል። ለአብነትም ከጌዴኦ ዞን፣ ከምዕራብ ጉጂ ዞን እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያጣቢያዎች የመጡ አይነታዊ መረጃዎች ለውይይቱ መነሻነት ቀርበዋል። የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን  መልሶ ለማቋቋም በተከናወነ ስራም በአበዛኛው ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ መሰራቱ ይታወቃል።። አሁንም ድረስ ስለቆዩት ተፈናቃዮችከመጠለያ ጣቢያዎች የተገኙ መረጃዎች እንዳሳዩት ጾታዊ ጥቃቱ እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ባሉ ህጻናት ላይም ጭምር እንደሚፈጸም ጠቁመዋል። በዚህ መነሻም ተወያዮቹ በተፈናቃዮች ዙሪያ የተቀመጡ የህግ ማዕቀፎች፣ የህገመንግስት ድንጋጌዎችና የአፈጻጸም ክፍተቶች ላይ መክሯል። አገራችን ሴቶችና ህጻናትን ለመንከባከብና ከጥቃት ለመከላከል በህገመንግስቱ አንቀጽ 30 እና 35 ማካተቷ እና በአፍሪካ ደረጃ የወጣውን የማፑቶ ፕሮቶኮል ስምምነትንም መፈረሟ ይታወሳል። አሁን ላይ መንግስት የአገር ውስጥ መፈናቀልን ህጋዊ መሠረት ባለው አግባብ ለመቆጣጠርና ለመደገፍ ሲልም ፖሊሲ እያዘጋጀ ይገኛል። መፈናቀል ሲኖር ሴቶችና ህጻናት ቀዳሚ ሰለባመሆናቸውና ወደ መጠለያ ከመግባታቸውም በፊት ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ በመሆናቸው በዚህ ላይ ሊሰራ ይገባል ነው የተባለው። ከመልሶ ማቋቋም ጋር ተያይዞም በተለይ ሴቶችና ህጻናት ከጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ልዩ ድጋፍ ይፈልጋሉ ተብሏል። ከመተከል ዞን የተፈናቃዮቹ ጊዜያዊ መጠለያ የመጡት ወይዘሮ ትርሃስ መዝገበ እንዳሉት ጾታዊ ጥቃቱን ለመቀነስ ከሰብዓዊ እርዳታ ጎን የህግና የፖሊሲ ጥበቃ መደረግ እንዳለበት ለኢዜአ ገልጸዋል። ድርጊቱም ሰው እያየው የሚፈጸም ባለመሆኑ የምርመራ ስርዓቱ አሰልቺና ለተጠቂዎች ድጋፍና ከለላ የሚሰጥ ባለመሆኑ መቀየር እንዳለበትም ተገልጿል። በውይይቱ ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን እንዚህ አካላትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በጥምረት ቢሰሩ ችግሩን ለመቀነስና መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል ነው የተባለው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም