በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የህዝብ ለህዝብ ውይይቶች መጠናከር አለባቸው

61
ኢዜአ፤ ህዳር 29/2012 በኢትዮጵያ በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተደራጀ አግባብ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ውይይት ማካሄድ ይገባል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የሐይማኖት አባቶች ገለፁ። በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለፁት ለኢትዮጵያ የማይበጅና ለህዝቦች ዘላቂ ሰላም የማይጠቅም የሴራ ፖለቲካ ይስተዋላል። እየተፈጠረ ባለው ሁኔታም በኢትዮጰያ ታሪክ ታይቶ የማያውቅና ባህልና ወጋችን በማይመጥን መንገድ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቅሰው  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሮችን ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉት ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል ። በተለይ ኢህአዴግን በማዋሃድ የተመሰረተዉ ብልጽግና ፓርቲ የበፊት ችግሮችን ቀርፎ አንድነትና ሰላምን፣ እኩል ተሳታፊነትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ተስፋዎችን ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል። እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ይስተዋሉ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች እየቀነሱ አንጻራዊ ሰላም እየተስተዋለ ነው ብለዋል፡፡ ይህን ለማስቀጠል ደግሞ በየደረጃዉ የህዝብ ለህዝብ ዉይይቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ የኦሮሚያና የአማራ፣ የትግራይና የአማራ አንዲሁም የሌሎች ህዝቦች ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም ያደረጓቸዉ ውይይቶች ተስፋ ሰጭ ዉጤት ያመጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸውን አመልክተዋል። ሁሉም በየደረጃው ጉልበቱን፣ እውቀቱንና አቅሙን አሳይቶ የመጨረሻ መፍትሄው ውይይት መሆኑን የተረዳ ይመስላል ያሉት ፕሮፌሰሩ የሀሳብ የበላይነት አሸናፊ እንዲሆን በጋራ ሊሰራ ይገባል ሲሉ አብራርተዋል። በዩኒቨርስቲው የዲሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሰብስብ አዲስ በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ካለችበት የመለያየትና ዉስብስብ ችግር እንድትወጣ ዋና መፍትሄው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውይይት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል ። አሁን የተጀመረዉ ምክክርና ውይይት ተስፋ ሰጭ በመሆኑ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ሁሉም በየትኛዉም ቦታ ሰርቶ የመኖር መብቱ እንዲከበር የየድርሻውን መወጣት አለበት። የዛሬውን አንጻራዊ ሰላም እንጂ ነገ ምን ሊከሰት እንደሚችል ፖለቲካው አያስተማምንም ያሉት ምሁሩ  ህዝቡ ግን የጋራ ማንነቱንና ሰላሙን  በማስጠበቅ መመከት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ጊዜያዊ መጅሊስ ፕሬዚዳንት ሼህ እንድሪስ በሽር በበኩላቸው ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የመከባበርና የመቻቻል ባህላችንን መጎልበት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ማንኛውም ሰው የራሱ መብት፤ ብሔርና ሐይማት እንዲከበር ከፈለገ የሌሎችን ማክበር እንደሚጠበቅበት መክረዋል ። ሐይማኖቶች መቻቻልን፣ አንድነትን፣ ፍቅርና መከባበርን አብዝተዉ ስለሚያስተምሩ ምዕምናን ፈጣሪና ራሱን ማስደት ከፈለገ እምነቱ የሚለዉን መተገብር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ አሁን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴም ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም በተሰማራበት መስክ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም