የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የዓይን ህክምና ማእከል አስገነባ

99
ኢዜአ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም  የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከኦርቢስ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያስገነባው የዓይን ህክምና ማእከል ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ሆስፒታሉ ገለፀ ። የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰላም አየለ በምረቃ ስንስርዓቱ ላይ እንዳሉት ማዕከሉ የተቋቋመው ከኦርቢስ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎትና ሌሎች ህክምናዎች ለመስጠት ነው ። ሆሲፒታሉ ለተለያዩ የዐይን ህመሞች ህክምና ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም የዐይን ቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚፈልጉ ህሙማን ግን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሲልክ መቆየቱን ጠቁመዋል። አገልግሎቱ መጀመሩ ህሙማን ለአይን ቀዶ ህክምና ወደ ሌላ አካባቢ ሲጓዙ ከሚደርስባቸው እንግልትና ተገቢ ያልሆነ ወጪ እንደሚታደጋቸው ተናግረዋል። ማዕከሉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የቅድመ ፍተሻ ስራ ሲያከናውን መቆየቱንና በዚህም 201 ህሙማን የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ማደረጉን ገልጸዋል። ሆስፒታሉ የዐይን ቀዶ ህክምናን ጨምሮ የአጥንት ስብራትና ሌሎች አዳዲስ የህክም አገልግሎቶችን በማስፋፋት ወደ ውጭ ሀገራት ለከፍተኛ ህክምና የሚላኩ የህሙማንን ቁጥር ለመቀነስ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል። የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ሲሳይ በበኩላቸው ማዕከሉ መከፈቱ የጌዴኦን ዞን ጨምሮ በአማሮና ቡርጅ አካባቢዎች ከአይን ጤና ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመቅረፍ ይሰራል። በማዕከሉ የታካሚዎች ማቆያን ጨምሮ መለስተኛና አጠቃላይ የዓይን ቀዶ ህክምና እንዲሁም ተመላላሽ የአይን ህክምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል። ኦርቢስ ኢትዮጵያ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በመመደብ ለህክምና ማእከሉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ከማሟላት ባሻገር 3 ስፔሻሊስት ሀኪሞችና ልዩ ስልጠና የወሰዱ 4 ነርሶች በስራው ተመድበው አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል ። የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ተወካይ አቶ መስፍን ዱቤ በበኩላቸው የአይን ቀዶ ህክምና ማዕከል በዲላ ሪፈራል ሆስፒታል መከፈቱ አገልግሎቱን በቅርበት ባለማግኘታቸው ይቸገሩ ለነበሩ ህሙማን እፎይታን ይሰጣል። የአይን ማዝ በሽታን ጨምሮ የአይን ሞራ ግርዶሽ፣ መንሸዋረር፣ የእይታ ችግሮች በዞኑ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል። የአይን ህክምና ማዕከሉ እነዚህንና ሌሎች የአይን ጤና ችግሮችን ለመፍታት የሚያከናውነውን ተግባር የዞኑ ጤና መምሪያ ያግዛል ብለዋል። በማዕከሉ የዐይን ህክምና አገልግሎቱን ካገኙ ታካሚዎች መካከል አቶ ሚሊዮን አለማየሁ እንዳሉት አይናቸው ላይ ይሰማቸው የነበረው ህመም ቀስ በቀስ የዐይን ብርሃናቸውን ስለከለለው እቤት ለመቀመጥ ተገድደው መቆየታቸውን ገልፀዋል ። በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል በቀኝ አይናቸው ላይ በተደረገላቸው የቀዶ ጥገና ህክምና ብርሃናቸው እንደተመለሰላቸውና የግራ አይናቸውን ለመታከም ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም