ረቂቅ አዋጁ ላይ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ ተዘጋጀ

61
አዲስ አበባ ሰኔ15/2010 የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም ስነ-ስርዓት ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ ተዘጋጀ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም ስነ-ስርዓት ረቂቅ አዋጅ ላይ የህዝብ አስተያየት መድረክ ዛሬ አካሂዷል። በመድረኩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ግለሰቦች፤ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ግለሰቦች ቤተሰቦችና ሌሎች የተገኙ ሲሆን ጠቅላይ አቃቢ ህግ ብርሃኑ ጸጋዬ በረቂቅ አዋጁ ላይ ገለጻ አድርገዋል። ረቂቅ አዋጁ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የህዝቡን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመጠበቅ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደወጣ ተገልጿል። ምህረትን በተመለከተ በወንጀል ህግ የተደነገገውን ከህገ-መንግስቱ ጋር በማጣጣም ምህረት የሚሰጥበትን ስነ-ስርዓት በህግ መደንገግ በማስፈለጉ እንደሆነም በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል። አዋጁ በማንኛውም የወንጀል አይነቶች ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾች ወይም ፍርደኞች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ቢገልጽም የሰው ዘር በማጥፋት፤ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ በመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር እና ኢ-ሰብአዊ የድብደባ ድርጊት መፈጸም ወንጀሎች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ያስቀምጣል። የወንጀል ድርጊቱ በአገር ሉአላዊነት ላይ የሚያስከትለው ወይም ያስከተለው ተጽእኖ ምህረት ለመስጠት ከግምት ውስጥ ከሚገቡ ሁኔታዎች ውስጥ ተጠቅሷል። በውይይቱ ከተገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተስተናግደው ጠቅላይ አቃቢ ህግ ብርሃኑ ጸጋዬ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል። በተለይም መንግስት በቅርቡ የህግ ታራሚዎችን በይቅርታና ክስ በማቋረጥ ከእስር እንዲፈቱ ማድረጉን ተሳታፊዎቹ በመልካም ጎን አንስተዋል። ረቂቅ አዋጁ ከህዝብ የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምሮ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም