ህገ መንግስቱ ብሔር ብሔረሰቦች በማንነታቸውና ቋንቋቸው እንዲኮሩ አድርጓል... ኢንጅነር አርአያ ግርማይ

92
ኢዜአ፤ ህዳር 29 / 2012 ዓ.ም ህገ መንግስቱ የብሔር ብሔረሰቦች ጭቆና ተወግዶ በማንነታቸውና ቋንቋቸው እንዲኮሩ ማድረጉን የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጅነር አርአያ ግርማይ ገለጹ ። "ህገመንግስታዊ ስርዓታችን  ለዘለቂ ሰላምና  ጥቅም "በሚል  መሪ ሀሳብ 14ኛው የብሔር ብሔረሰቦች  በዓል  ዛሬ በመቀሌ ከተማ  ተከብሯል። የአስተዳደሩ ከንቲባ በበዓሉ ስነስርዓት ወቅት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ለዘመናት ተንሰረፍቶ የነበረውን የብሔር ብሔረሰቦች ጭቆና ከተወገደ ወዲህ በቋንቋቸው መማርና መዳኘት ችለዋል። "በማንነታቸውና በእምነታቸው እንዲኮሩ ያደረገ ህገ መንግስት ባለቤት የሆኑበትን ህዳር 29 በየዓመቱ በልዩ ሁኔታ ይከበራል" ብለዋል። ብሔር ብሔረሰቦች  ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩና አካባቢያቸውን እንዲያለሙ በመደረጉ   ለሀገሪቱ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ    ማበርከቱን  ኢንጂነር አርአያ  ተናግረዋል። "ባለፉት 27 ዓመታት አንዳ አንድ  ኃይሎች እንደሚሉት ሳይሆን ብሔር ብሔረሰቦች  አስተማማኝ ሰላምና ልማት እንዲጎናፀፉ ያስቻለ ነበር "ብለዋል። ከንቲባው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ህገመንግስቱና ፌደራላዊ ስርዓቱ ለመናድ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ብሔር ብሔረሰቦች ጥብቅና ሊቆሙለት ይገባል። ብሔር ብሔረሰቦች እንድነታቸው በማጠናከር ልማትን ማስቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በበዓሉ ከተሳተፉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  ወጣት  ሃፍታሙ ወልደገብርኤል በሰጠው አስተያየት "የትግራይ ህዝብ ከብሔር ብሔረሰቦች  ጋር በመሆን በከፈለው መስዋዕት የተገኙ በርካታ ውጤቶች ዘላቂ ማድረግ ይገባል" ብለዋል። አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረው የሰላም እጦትና ተንቀሳቅሶ የመስራት ችግር እንዲፈታ ብሔር ብሔረሰቦች ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክቷል። "የብሔር ብሔረሰቦች በዓል  የተደበቁ ማንነቶች ጎልተው በአደባባይ እንዲወጡ ያስቻለ  ነው "ያሉት  ደግሞ ሌላዋ የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ፃድቃን ለገሰ ናቸው። ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረውና ተፈቃቅደው ባለፉት ዓመትት በሀገሪቱ ልማት እንዲመጣ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ማስቀጠል እንዳለባቸውም  ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም