የአገሪቱን የሰላም እጦት ችግር ለመፍታት የጋሞ አባቶችን የሰላም እሴት ማስፋት ይገባል

100
ኢዜአ ህዳር 29 / 2012 በአገሪቱ የሚስተዋለው ወቅታዊ የሰላም እጦት ችግር እንዲፈታ የጋሞ አባቶች የሰላም እሴትን ማስፋት እንደሚገባ ተጠቆመ። “አብሮነት ከጋሞ እስከ ጎንደር” በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የጉዞ ፕሮግራም ለማድረግ መታቀዱም ተመልክቷል፡፡ የሰላም ጉዞውን ያዘጋጀው የ"ህብረመንጎል መልቲ ሚዲያ" ዳይሬክተር ወይዘሪት ቤዛ ነጋሽ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው የሰላም እጦት ችግር እንዲፈታ የጋሞ አባቶችን የሰላም እሴት ወደሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ማስፋት ይገባል። ለእዚህም የጋሞ አባቶች ግጭት ከመፈጠሩ በፊት እንዴት ማብረድ እንደሚቻል የፈጸሙትን የሰላም ገድል ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለማስተላለፍ ከአርባ ምንጭ እስከ ጎንደር አገር አቀፍ የጉዞ ፕሮግራም እንደሚደረግ አመልክተዋል። ከጥር 4 እስከ 14 ቀን 2012 ዓ.ም በሚደረገው ጉዞ 150 ልዑካን ያሉት ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎችና የወጣት ተወካዮች እንዲሁም የመንግስት አካላት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። እንደወይዘሪት ቤዛ ገለጻ ጉዞው በአገሪቱ ያሉ በርካታ ከተሞችን አቋርጦ ስለሚያልፍ በእነዚህ አካባቢዎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላሉ ተማሪዎች በሰላም፣ በአብሮነት፣ በመቻቻልና በአገር ፍቅር ዙሪያ የማነቃቂያ ምክር ይሰጣቸዋል፡፡ በተጨማሪም በሻሸመኔ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ መቀሌና ጎንደር ከተሞች በሰላም እሴቶች ላይ ውይይትና የልምድ ልውውጥ ከህብረተሰቡ ጋር እንደሚደረግ ተናግረዋል። የጋሞ ዞን አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሰግድ ተረፈ በበኩላቸው እንዳሉት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ይሁንና በጋሞ መካሪ አባቶችና ሰሚ ልጆች በተደረገ የጋራ ጥረት በዞኑ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ አገራችን ካለችበት ወቅታዊ የሰላም ችግሮች ለማውጣት የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ወሳኝ ቢሆንም የአገር ሽማግሌዎች የአስታራቂነት ሚና ተኪ የሌሌው መሆኑንም አቶ አሰግድ ተናግረዋል፡፡ "ያለሰላም የሰው ልጅ የመኖር ህልውና የሚታሰብ ባለመሆኑ የራሳችንን ችግር በአገሪቱ ባሉ ቱባ የግጭት አፈታት ባህሎች ለመፍታት መታቀዱ መልካም ተግባር ነው" ብለዋል። በጉዞ ፕሮግራሙ የሚከናወኑ ተግባራት በህዝቦች መካከል መቀራረብና አንድነት እንደሚያመጣ ጠቅሰው ኢትዮጵያዊ ይዘት ያላቸውን የፍቅር፣ የይቅርታና የመቻቻል ባህል ለማዳበር ዜጎች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም