ሱዳን ለኬንያ እና ታንዛኒያ የሽብር ሰለባዎች ካሳ ልትከፍል እንደሆነ ተገለፀ

70

ኢዜአ፤ህዳር 29/2012 ሱዳን እ.ኤ.አ በ 1998 በናይሮቢ እና በዳሬሰላም የአሜሪካ ኤምባሲ በደረሰው ፍንዳታ ለተጎዱ ቤተሰቦች የገንዘብ ካሳ ለመክፈል ቃል መግባቷ ተገልጿል።

 የዎል ስትሪት ጆርናልን ዘገባ ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ እንደዘገበው ሱዳን ላደረሰችው ጉዳት 10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ካሳ እንድትከፍል በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች እንደተወሰነባት የጠቆመው ዘገባው ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ 5.9 ቢሊዮን ዶላር ከአደጋው ለተረፉ ቤተሰቦች እንዲሰጥ ተወስኗል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላ ሃምዶክ ከዎል ስትሪት ጆርናል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አገራቸው በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ካሳውን እንደምትከፍል ገልፀዋል ፡፡

ሆኖም የተጎጂ ጠበቆች ይህ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ የኬንያ ዴይሊ ኔሽን  ጋዜጣ በመጥቀስ በመረጃው ተዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላ ሃምዶክ አሜሪካ ሱዳንን ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ እንድትሰረዝ የመጀመሪያውን ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው ከዎል ስትሪት ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት።

ሱዳን ከአሜሪካ ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ምክክር ካካሄደች በኋላ ከዝርዝር ውስጥ ለመውጣት አብዛኞቹን መስፈርቶችን እንዳሟላች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሁለት ጉዳዮች ሁለት ዋና ዋና እንቅፋቶች እንደቀራቸው ተናግረው ከአሸባሪው ጥቃቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መፍታት እና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከአሜሪካ ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የሱዳን መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ ሱዳን ለአለም አቀፍ ህጎች ያላትን  ቁርጠኝነት በተግባር መሆኑንና  ይህም የምኞት ቃል ብቻ እንዳልሆነ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም