አዲሱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር የሜዳ ላይ ስርዓት አልበኝነት ችግርን መፍታት ቅድሚያ ስራው ሊሆን ይገባል-የስፖርት ጋዜጠኞች

84
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲሱ አመራር ውድድር በሚካሄድበት ወቅት የሚከሰተውን የሜዳ ላይ ስርዓት አልበኝነት ችግርን ቅድሚያ በመስጠት መፍታት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ የስፖርት ጋዜጠኞች ገለጹ። በተደጋጋሚ ሲራዘም የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንታዊና የሌሎች ስራ አስፈጻሚዎች ምርጫ ባለፈው ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ተካሂዶ እልባት ማግኘቱ ይታወሳል። ፌዴሬሽኑ ውጤታማ ተግባራትን ማከወን ይችል ዘንድ የሜዳ ላይ ስርዓት አልበኝነት መስመር የማስያዝ ስራ ቀዳሚ ስራው ሊሆን ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የስፖርት ጋዜጠኞች ተናግረዋል። በኢትዮ ኤፍኤም ራዲዮ የስፖርት ጋዜጠኛ የሆነው ኃይለእግዚብሄር አድሃኖም አዲሱ አመራር ለመጪዎቹ ረጅም ዓመታት በበጎ መልኩ ሊነሳ የሚችል አሻራ ጥሎ ማለፍ አለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋር በተያያዘ የሚታዩ ስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶችን በማሻሻል የስፖርቱን ቤተሰብና ዘርፉን ጠንካራ የኃብት ምንጭ ለማድረግ ብስለት የተሞላበት አመራር ሊፈጠር እንደሚገባ ገልጿል። ይህ ከሆነ ደጋፊ የሜዳ ላይ ረብሻ ፈጣሪ ሳይሆን ትልቅ የፋይናስ አቅም ማጠናከሪያ እንደሚሆንም ጠቁሟል። በፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት የስፖርት ጋዜጠኛ አወቀ አብርሃም ከሁሉም በፊት መቀረፍ ያለበት ችግር የእግር ኳስ ሜዳ ላይ እየተባባሰ የመጣው ስርዓት አልበኝነት እንደሆነ ገልጿል። የሜዳ ላይ ስርዓት አልበኝነት ዋና ችግር እግር ኳስ የመደገፍ ባህሉ ደካማ በመሆኑ የሚከሰት እንደሆነ የሚገልጸው ጋዜጠኛ አወቀ ችግሩ ጎልቶ የሚታየው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያድጉ የክለቦች ደጋፊዎች ዘንድ እንደሆነ ጠቁሟል። በዚህ ረገድ ለሚስተዋለው ችግር ሁሉም በየደረጃው ኃላፊነት መውሰደ ያለበት ቢሆንም ደጋፊዎች ሲያጠፉ እስከ ነጥብ ቅነሳ የሚደርስ እርምጃ በክለቡ ላይ ለመውሰድ የሚያስችል አሰራር ጭምር ሊፈጠር እንደሚገባም ጠቅሷል። የሚወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የፌዴሬሽኑ የዲሲፒሊንና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ የሚሰራበት ስርዓት መፍጠር የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድቷል። በሀትሪክ ስፖርትና ሊግ ጋዜጣ እየሰራ የሚገኘ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በበኩሉ እግር ኳሱን ለማሳደግ  ከሁሉም በላይ ተግባብቶ መስራት ወሳኝ እንደሆነ አስምሮበታል። አዲሱ አመራር ከቢሮ ሥራ ይልቅ በሜዳ ላይ ለሚከናወኑ ስልጠናዎች፣ ክትትልና ድጋፍ የበለጠ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል። እነዚህ ችግሮች ከተፈቱ በኋላ  ከባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ መስራትና አደረጀጀቱን ማዘመን ተከታዩ ስራቸው ሊሆን እንደሚገባም አያይዘው ገለጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም