በድሬደዋ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ለመቆጣጠር ርብርብ ይደረጋል- የከተማዋ ምክትል ከንቲባ

79
ኢዜአ ህዳር 29/2012 በድሬዳዋ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ለመቆጣጠርና ሶስቱን ዘጠናዎች ለማሳካት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግ የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ገለፁ ። የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት የኤች አይቪ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝባቸው ሰዎች መካከል ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ወደ ህክምና ተቋማት እንዲመጡ የተቀናጀ ርብርብ ይደረጋል ። የፖለቲካ አመራሩም ሴክተር ዘለል ለሆነው ችግር የመከላከል ስራውን በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በሀገር ደረጃ የኤች አይቪ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው በሚገኙ ማህበራት፣ ሴክተሮችና ተቋማት ባከናወኑት የተቀናጀ ተግባር አበረታች ውጤቶች ተገኝቷል፡፡ በድሬዳዋም በሁሉም መስክ በተሰሩ የህዝብ የግንዛቤ ንቅናቄና ህክምናን ተደራሽ የማድረግ ሥራዎች ውጤት ቢመጣም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመከላከሉ ባህል እየቀነሰ ይገኛል ብለዋል፡፡ በአሁን ሰዓት በቫይረሱ ስርጭት በሶስተኛ ደረጃ በምትገኘው ድሬዳዋ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የፖለቲካ አመራሩ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ገልፀዋል ፡፡ በበጀት ውስንነት የሚፈለገውን ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ማድረግ ባይቻልም ማህበረሰቡን በማስተባበር ጉዳዩን ግንባር ቀደም አጀንዳው እንዲሆን እየተደረገ ይገኛል ያሉት ምክትል ከንቲባው አዲሱ ትውልድ ስለ ቫይረሱ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲኖረው በሁሉም የትምህርት ደረጃ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል ። እንደ ምክትል ከንቲባው ገለፃ በተለይ ስለቫይረሱ በሚሰጥ ግንዛቤ በመታገዝ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ካለባቸው ሰዎች 90 በመቶ የሚሆኑት እንዲመረመሩ ፣ ከተመረመሩት 90 በመቶ መድሃኒት መውሰድ እንዲጀምሩና ከእነዚህ ደግሞ 90 በመቶ መድሃኒቱን በትክክል እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ። እ.ኤ.አ. በ2020 ሶስቱን ዘጠናዎች በማሳካት ከኤች አይቪ ነጻ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተመሣሣይ አለም አቀፍ የኤች አይቪ ቀን ምክንያት በማድረግ በተደረገው ውይይት ላይ ሻማ ብርሃን የፀረ-ኤች አይቪ ማህበር መሪ ወይዘሮ ውቢት አድማሱ አንደገለፁት ቫይረሱ በደማችን ለሚገኝ ሰዎች ለሚደረገው ክብካቤና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ። ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት ማህበራት ጥምረት በመፍጠር በገጠርና በከተማ በመዘዋወር ወጣቶችን፣ እናቶችን፣ ሴቶችን፣ የትምህርት ቤቶችንና ህዝቡ እንዲመረመሩና ጤናቸውን እንዲጠበቁ እያስተማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሞት ቢቀንስም አሁንም የኤች አይቪ ስርጭት አለ ያሉት ወይዘሮ ውበት ቫይረሱ ባለበት እንዲቆም በወጣቶች ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ‹‹እኛ ወጣቱን ለማስተማር ሁሉግዜም ዝግጁ ነን››ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ውቢት ገለፃ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አባላቶቻቸው የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት በመጠቀምና የህክምና ባለሞያዎችን ምክር በመከተል 25 ዓመት ሙሉ ያለችግር እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ፡፡ በዕለቱ የቫይረሱን ስርጭትና ህክምና ተደራሽነት አስመልክተው ፅሁፍ ያቀረቡት አቶ ሀሰን ቡሽራ እንደተናገሩት  በድሬዳዋ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ኤች አይ ቪ በደማቸው እንዳለ ቢገመትም ህክምናውን እየተከታተሉ የሚገኙት ግን 7 ሺህ ብቻ ናቸው ፡፡ ይህም የሶስቱን ዘጠናዎች ተልዕኮ ማሳካት ላይ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ወደ ህክምና እንዲመጡ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም ራሱንና ቤተሰቡን በመጠበቅ፣ በቫይረሱ የተጎዱትን በመደገፍና በመርዳት ችግሩን በጋራ መከላከልና መቆጣጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም